AMN – የካቲት 15/2017 ዓ.ም
የአህጉሩን የቡና አቅም የሚያሳድጉ ምርምሮችንና ትብብሮችን የሚያጠናክሩ ውሳኔዎችን አሳልፈናል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
በታንዛኒያ ዳር-ኤስ-ሰላም ከተማ የተካሄደው 3ኛው የG25 የአፍሪካ የቡና ጉባኤ የአህጉሩን የቡና አቅም የሚያሳድጉ ምርምሮችንና ትብብሮችን የሚያጠናክሩ ውሳኔዎችን አሳልፈናል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኮፊ አረቢካን ጨምሮ ዓለም ላይ ተፈላጊ የሆነ ባለ ልዩ ጣዕምና ጠንካራ የቡና ምርት መገኛው በአህጉራችን አፍሪካ ነው ብለዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ ቀዳሚ የቡና አምራች ሀገር እንደመሆኗ ከዘርፉ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ ሰፊ የሪፎርም ስራዎችን በመተግበር ውጤት እያመጣች ትገኛለች ብለዋል፡፡

”የአፍሪካ የቡና ኢንዱስትሪን በማነቃቃት ለወጣቶች የሥራ ዕድሎችን መክፈት” በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው ጉባዔ፣ ዘርፉን ለማነቃቃትና ሰፊ የስራ ዕድል ለመፍጠር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውንም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ በጉባኤው ባቀረበችው ጥያቄ መሰረት አራተኛው የG25 የአፍሪካ የቡና ጉባኤ በ2019 ዓ.ም በአዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ እንዲካሄድ የተወሰነ መሆኑን የገለጹት አቶ ተመስገን፣ ለኢትዮጵያ የተሰጠውን ዕድልም በታላቅ ኃላፊነት መቀበላቸውን በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት ገልጸዋል፡፡