AMN- ጥቅምት 27/2017 ዓ.ም
የጊኒው ጠቅላይ ሚኒስትር አማዱ ኡሪ ባህ በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለውን አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በሀገራቸው ለመተግበር ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) ጋር በሀገራዊ እና አህጉራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
በውይይቱ ወቅትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው አረንጓዴ አሻራ ውጤታማ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ይህንንም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በሀገራቸው የመተግበር ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸውንም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ልማት እና በተለያዩ መስኮች ያላትን ልምድ እና ተሞክሮ ወደ ጊኒ መውሰድ እንደሚፈልጉ በመግለጽ ለዚህም አስፈላጊው የቴክኒክ ድጋፍ እንዲደረግላቸው መጠየቃቸውም ተመላክቷል።
ሁለቱ ሀገራት ከአሁን በፊት በበርካታ መሥኮች የተፈራረሟቸውን ጉዳዮች ወደ ተግባር ለማስገባት በትብብር መሥራት እንደሚገባም አንስተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች ለጊኒ ያላትን ተሞክሮ ለማካፈል ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።
አረንጓዴ አሻራ በኢትዮጵያ የውኃ ሃብት ዳግም እንዲያንሰራራ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እ.ኤ.አ. 2020 በጊኒ ያደረጉት ጉብኝት ታሪካዊውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረ መሆኑንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።