የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና እውን የማድረግ ሂደት ውስጥ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ሚና ከፍተኛ ነው- ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)

You are currently viewing የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና እውን የማድረግ ሂደት ውስጥ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ሚና ከፍተኛ ነው- ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)

AMN – ሚያዝያ 15/2017 ዓ.ም

በብልፅግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዘርፍ አስተባባሪነት “የድህረ እውነት ዘመንን በእውቀትና በእውነት” በሚል መሪ ቃል ለኦሮሚያ ክልል አመራሮች እና የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ባለሙያዎች የተዘጋጀ ስልጠና በባቱ ከተማ መሰጠት ተጀምሯል፡፡

የብልፅግና ፓርቲ ዋና ፅ/ቤት የህዝብና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፤ በስልጠናው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር የተገኘውን ድል እና ስኬት የድህረ እውነት ዘመን በተረዳ ኮሙኒኬሽን በእውነትና በእውቀት ተጠቅመን በማስቀጠል የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግና እውን የማድረግ ሂደት ዉስጥ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።

አሁን ባለንበት በድሀረ እውነት ዘመን የኢትዮጵያን ከፍታ የማይፈልጉ አፍራሽ ሃይሎች ስሜት ቀስቃሽ ንግግሮች በመጠቀም ባለፉት ሰባት የለውጥ አመታት ውስጥ የተመዘገቡ ድሎችና ስኬቶችን ለማራከስ፣ ኢትዮጵያን ለመበታተን እየሰሩ ነው ያሉት ቢቂላ (ዶ/ር) ይህን የጥፋት ሃይል በእውነትና በእውቀት በመመከት እውነተኛ መረጃዎችን ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ከፊያለው ተፈራ በበኩላቸው፤ የድህረ እውነት ዘመን እጅግ አደገኛ በሆነ ሁኔታ እያደገ በመሆኑ ይህን በአግባቡ የተረዳና ፈጥኖ የሚላመድ ኮሙኒኬተር ያስፈልጋል ብለዋል።

የብልፅግና ፓርቲ እሴቶች፤ መርሆች እና እሳቤን በሚገባ መልኩ በማስተዋወቅ ገዢ ትርክትን ለማስረፅ በትኩረት መስራት እንደሚገባ መናገራቸውን ከብልፅግና ፓርቲ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review