የኢትዮጵያ አየር ኃይል ተልዕኮውን በአስተማማኝ ሁኔታ የተወጣና የሀገር ህልውናንም በጀግንነቱ ያፀና ነው ሲሉ የኢፌዴሪ አየር ሃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ።
ዋና አዛዡ በአቭዬሽን ሙያ ተቋሙን ለማገልገል ወደ አየር ኃይል አካዳሚ ለስልጠና የተቀላቀሉ ምልምል የሰራዊት አባላትን በአየር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ ተቀብለው አነጋግረዋል።
ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የተጣለበትን ተልዕኮ በአስተማማኝ ሁኔታ በመወጣት የሀገር ህልውናንም በጀግንነቱ ያፀና ተቋም መሆኑን ገልዋል።
ተቋሙ በዚህ ሁሉ የታሪክ ጉዞ ውስጥ ከራሳቸው ይልቅ ሀገር ያስቀደሙና ለኢትዮጵያ ክብር ሲሉ የተዋደቁ ታላላቅ ጀግኖችን ያፈራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሰልጣኞቹ ተልዕኳቸውን በፅኑ ሊረዱ እንደ ሚገባ ያስታወቁት ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፣ በቀጣይም ከወታደራዊ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት እስከ አየር ኃይል አካዳሚ ድረስ በተዋረድ የሚሰጡትን ስልጠናዎች በብቃት ለማጠናቀቅ ራሳቸውን በስነ ልቦና ብሎም በአካል እና አእምሮ ብቁ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በዕለቱ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አካዳሚ በቅርቡ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች እና የከተማ መስተዳድር መልምሎ መስፈርቱን ያሟሉ ሰልጣኞችን በአቭዬሽን ሙያ ዘርፍ ወደፊት ተቋሙን እንዲያገለግሉ በተያዘው እቅድ መሠረት ለማሰልጠን ወደ አየር ኃይል አካዳሚ ያስገባ መሆኑም መገለጹን ከመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።