የከተማዋን ልማት ለማፋጠን ሁሉም የንግዱ ማህበረሰብ አካላት የተለየ ሀላፊነት አለባቸው፡- አፈ ጉባኤ ቡዜና አልከድር

AMN – ጥር 8/2017 ዓ.ም

ከተማችን የሀገራችን ርዕሰ መዲና እንደመሆኗ መጠን ልማቷን ለማፋጠን ሁሉም የንግዱ ማህበረሰብ አካላት በተለየ ሁኔታ ከፍተኛ ሃላፊነት እንዳለባቸው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ቡዜና አልከድር አስታወቁ ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት 18ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በአድዋ ድል መታሰቢያ አዳራሽ አካሂዷል።

በጉባኤው ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ቡዜና አልከድር የንግድ ምክር ቤቱ የዘርፉን ተዋንያን በማስተባበር፣ ከተማችን ለንግድ ሥራና፣ ለሥራ ፈጠራ እንዲሁም ለኢኮኖሚ ልማት እድገት አመቺነቷ የተረጋገጠ የኢንቨስትመንት ማዕከል እንድትሆን የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ከተማችን አሁን አሁን በተለይ፣ በፈጣን ልማትና የብልጽግና ጉዞ ላይ እንደመሆኗ መጠን ፤ ለንግድ ስራ እንቅስቃሴና ለግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ከምን ጊዜም በላይ ምቹ ምህዳር ተፈጥሯል ብለዋል፡፡

ስለሆነም ከእናንተ ከንግድ ምክር ቤቶች እና ከዘርፉ ተዋንያን ጋር በመሆን፣ ይህንን መልካም አጋጣሚ ለላቀ ልማታዊ ድልም መጠቀም የግድ ይላል ብለዋል፡፡

በጉባኤው የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅን ጨምር በርካታ የዘርፉ አመራሮች እና አባላት መታደማቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review