
AMN-ታህሳስ 5/2017 ዓ.ም
የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን ከማስዋብ ባለፈ ለአረንጓዴ ልማት ትኩረት የሰጠ፣ የህዝብን ጥያቄ በአፋጣኝ የመመለስ ባህልን እያጎለበተ የመጣ ተግባር ነው ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ገለጹ።
አቶ ሞገስ ባልቻ በቂርቆስ፣ በየካ፣ በጉለሌና በአራዳ ክፍለ ከተሞች እየተተገበረ ያለውን የኮሪደር ልማትና የወንዝ ዳር ፕሮጀክት አፈፃፀም ገምግመዋል።
የወሰን ማስከበር፣ የካሳ ክፍያ፣ የምትክ ቦታና ቤት አፈፃፀም፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታና የሰርቬይንግ ስራ ፣ የላንድ እስኬፕ ስራዎች እና ሌሎች ተግባራት በግምገማቸው ትኩረት የተደረጉባቸው ጉዳዮች መሆናቸው ተገልጿል።
አጠቃላይ የስራዎች አፈፃፀም ሪፖርት በየዘርፉ ቀርቦ የተገመገመ ሲሆን ስራዎች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ መሰረት እየተሰሩ መሆናቸውን ከቀረቡት ሪፖርቶች፣ ከመስክ ድጋፍና ክትትል ማስተዋል መቻሉን አቶ ሞገስ ገልፀዋል፤
የኮሪደር ልማቱም ሆነ የወንዝ ዳር ፕሮጀክቱ ከተማዋን ከማስዋብ ባለፈ ለአረንጓዴ ልማት ትኩረት የሰጠ፣ የህዝብን ጥያቄ በአፋጣኝ የመመለስ ባህልን እያጎለበተ የመጣ ተግባር በመሆኑ ይህንኑ ማስቀጠል ከአመራሩና ከዘርፉ ባለሙያዎችና ከአማካሪዎች ይጠበቃል ብለዋል አቶ ሞገስ በግምገማው ወቅት።
ስራውን በተጀመረው ፍጥነት ለማስቀጠል መቀናጀት ያስፈልጋል ያሉት አቶ ሞገስ የከተማ አስተዳደሩ ለህዝብ የገባውን ቃል ከሚተገብርባቸው መንገዶች አንዱ የሆነውን ሁለተኛውን ዙር የኮሪደር ልማት አጠናቆ ባለቤት ለሆነው ህዝብ ለማስረከብ ሁሉም ዘርፍ ስራውን በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
በቀጣይ የካሳ ክፍያና የምትክ ቦታን በተመለከተ የከተማውን አቅም ታሳቢ ባደረገ መልኩ ማፋጠን፣ የመሰረተ ልማት ዘርፉን ማቀናጀት፣ ለየዘርፉ ተግባር ትኩረት መስጠት፣ ሁሉም የተሰጠውን ስምሪት በብቃት መወጣት ከአመራሩም ሆነ ከዘርፉ ባለሙያዎችና አማካሪዎች እንደሚጠበቅ አቶ ሞገስ ማሳሰባቸውን ከብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።