የውስጥ ጥንካሬ እና ዐቅም ለውጭ ግንኙነት ስኬታማነት ፋይዳው የላቀ ነው- የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

You are currently viewing የውስጥ ጥንካሬ እና ዐቅም ለውጭ ግንኙነት ስኬታማነት ፋይዳው የላቀ ነው- የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

AMN – ሚያዚያ 2/2017

ለውጭ ግንኙነት ስኬታማነት የውስጥ ጥንካሬ እና ዐቅም ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ገለጹ።

“ዓላማ ተኮር ተግባቦት ለኢትዮጵያ መንሰራራት” በሚል መሪ መልእክት ለኮሙኒኬሽን ዘርፉ የክልል እና ከተማ አስተዳደር መዋቅር አመራሮች እና ከፍተኛ ባለሙያዎች ሥልጠና እየተሰጠ ነው።

ጂኦ-ፖለቲካዊ ዓውዶች እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ያተኮረ ስልጠናም ተሰጥቷል።

ሥልጠናውን የሰጡት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ ውስጣዊ ዐቅሞችን ማጎልበት ለውጭ ግንኙነት ስኬታማነት የላቀ ሚና ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ረገድም የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ዐቅሞቹን ለማጎልበት የተቀረጹ ፖሊሲ እና ስትራቴጂዎችን ማስገንዘብና ማስረጽ ላይ በትኩረት እንዲሰሩ አሳስበዋል።

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን፣ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን፣ የመንግሥት መነሣሣቶችን በአግባቡ ማስገንዘብ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም ቀፋዊ አዝማሚያዎችንና አንድምታቸውን የተመለከቱ ወቅታዊና ሚዛናዊ መረጃዎችን መስጠት ለሀገራዊ ገጽታ መገንባት እና ለዲፕሎማሲ ስኬት ፋይዳቸዉ ጉልህ መሆኑን አመልክተዋል።

በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሥራዎች የተቀናጁ፣ የተደራጁ እና ወቅታዊ መረጃዎችን በመስጠት ዜጎች የሀገራቸውን መሻትና ዕቅድ ተገንዝበው በተሰማሩበት መስክ ሁሉ ዲፕሎማት እንዲሆኑ ማስቻል ይገባል ብለዋል፡፡

አዲሱ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ እሳቤ ወቅታዊ ነባራዊ ዓውዱን ያገናዘበ፣ ለኢትዮጵያ ሕልሞች መሳካት ከውስጥ ወደ ውጭ የሚያይ እና ቅድሚያ ለጎረቤት የሰጠ መሆኑን ነው የገለጹት።

በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በተለያዩ ሀገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መደረጉም የዚሁ ማሳያ ነው ብለዋል።

የሥልጠናው ተሳፊዎች በበኩላቸው ለዘርፉ በተከታታይ እየተሰጡ ያሉ የፖሊሲ እና የዐቅም ግንባታ ሥልጠናዎች ጥልቀት ያለው ግንዛቤ እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።

ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ በመስጠት የሕዝቡን የመረጃ ፍላጎት ለማሳካት ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረ መናገራቸውን የአገልግሎቱ መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review