ታላቁ ፈላስፋ፣ ባለቅኔ፣ ደራሲና ሰዓሊ ካህሊል ጂብራን የሰዎችን የህይወት ገጽ በፈርጅ በፈርጁ ገልጦ ያስነበበ ጥልቅ አሳቢና ከያኒ ነው፡፡ በሥነ ጽሑፋዊ ስራዎቹ ውስጥም እጅግ በተመረጡ ውብ ቃላት ስለ ሕይወት ወጣ ያሉ ምልከታዎችን መፈንጠቅ የቻለም ነው። ጥበብ፣ ርህራሄ፣ እውነት፣ ፍቅር፣ ውበት፣ ተፈጥሮ… በስራዎቹ ጎልተው የሚንጸባረቁ ነገረ-ጭብጦች ናቸው፡፡
ጂብራን በተለይ ‘The Prophet’ በተሰኘው ውብ ድርሰቱ እነዚህን ጭብጦች ጥበብና ውበት በተሞላበት አኳኋን ፈልቅቆ እንዲያሳይለት አንድ ተወዳጅ ገጸ-ባህሪ መለመለ። ይህ ገጸ-ባህሪ “ጠቢቡ” ይሰኛል፡፡ በአንድ ገጹ ተማሪ በሌላ ገጹ መምህር ነው። ታዲያ ጠቢቡ ሁሉም ሰው ዘንድ በመሄድ ዕውቀትን ይቀስማል፡፡ የቀሰመውን ዕውቀት ውብ አድርጎ ይተርካል። ግርባብም ልክ እንደ ጠቢቡ ነው። ከሁሉም ዘንድ ተጉዞ ዕውቀትን የሚቀስም፤ ከህይወት ልምድ የሚማር መምህርም፤ ተማሪም፡፡ በዚህ ጽሑፍም ‘ያ ደግ ሰው ግርባብ’ የተሰኘው የደራሲ ፍቃዱ አየልኝ መጽሐፍ ላይ የግርባብን ዱካዎች በመከተል የጠቢቡን ዕይታዎች በጨረፍታ እናስቃኛችኋለን፡፡
‘ያ ደግ ሰው ግርባብ’ ሊሞግተን የመጣ መምህር ነው፡፡ እንድናስተውልና ራሳችንን መልሰን እንድናይ ሊያነቃን የመጣ መምህር ነው፡፡ ማህበረሰባዊ ዕሴቶቻችንን በአንክሮ እንድናጤናቸውና እንድንጠብቃቸው ሊያሳስበን የመጣ የህይወት መምህር፡፡ ያ ደግ ሰው ራሱን ግን እንደ መምህር አይቆጥርም፡፡ ‘መምህር ነኝና ላስተምራችሁ’ አይልም፡፡ ያ ደግ ሰው ካገኘው ሰው ሁሉ ለመማር፣ ከተለያዩ የህይወት መንገዶች አንዳች ቁም ነገር ለመገብየት ነው ልፋትና ጥረቱ፡፡ በብያኔና በፍረጃ ያልተቃኘ ነው፤ መምህርነቱ፡፡ ያወቀውንና ያነበበውን በሌሎች ላይ ለመጫንም አይከጅልም፡፡
ደራሲው የድርሰቱ አብይ ገጸ-ባህሪ አድርጎ ያጨው ያ ደግ ሰው ግርባብ፣ የህይወት ቀለም አንድ ወይም ሁለት ብቻ ሳይሆን ህብራዊ መሆኑን በመኖር ውስጥ ገልጦ ያሳየናል፡፡ ያስተምረናል፡፡ ያ ደግ ሰው ማህበረሰባዊ ተዋረዶችን ወደ ጎን በማድረግ ሁሉም’ጋ ትምህርት መኖሩን በግብሩ ገልጦ ይነግረናል፡፡
ያ ደግ ሰው በሰርካዊው የህይወት ሩጫችን ችላ ያልናቸው ግለሰቦች ዘንድ ተጉዞ ነው ሥለ ህይወት የሚጠይቃቸው። እረኛ፣ ድንጋይ ጠራቢ፣ የአሞሌ ጨው ነጋዴ፣ ዕጣን ሰፍራ የምትሸጥ ሴት፣ ገበሬ፣ አዝራር ሰሪ… ተጠይቀው የህይወት አተያያቸውን ይመልሳሉ። በመጽሐፉ ውስጥ እንስሳትና ነፍሳትም ቦታ አግኝተው ስለራሳቸው፣ ስለአካባቢያቸውና ሥለ ህይወታቸው ይተርካሉ፡፡ እንስሳትን በገጸ-ባህሪነት መልምሎ እንዲተርኩ፤ ሰውና ህይወትን እንዲያሄሱ በደራሲው ታጭተዋል፡፡ ታዲያ ደራሲው እንስሳቱ ሳይጫናቸውና ሳይፈርጃቸው ነው በነጻነት እንዲተርኩ፤ ህይወትን እንዲሄሱ ያደረገው፡፡
“ያ ደግ ሰው ወደ ዕጣን መሸጫ፣ ሉባንጃ፣ ቡክቡካ ወዳለበት፣ አሪቲ፣ ጠጅ ሳር ወደ ተጎዘጎዘበት ሱቅ አመራ፡፡ ዕጣን የምትሰፍረውንም ሴት፡ ‘ሰላም ላንቺ ይኹን መዐዛን የምትሰሪ!’ ኑሮ እንዴት ይዞሻል?” አላት
ያቺ ሴትም፡ “ይኸው ነው ጋሼ፣ ኑሯችን ጥሩ ዕጣን ይመስላል፡፡ ሲቃጠል ጥሩ ይሸታል፡፡ ኑሮዬ በቁመቱ ምሬት ከአፉ ንዴት ከፊቱ አይታይበትም…” አለችው፡፡
ያ ደግ ሰው፡ “በሣቅ ውስጥ ስላለ ኩርፊያ፣ በብርሃን ውስጥ ስላለ ጨለማ ትንሽ ንገሪኝ” አላት፡፡… (ገጽ፣38)
እንዲህ እንዲህ እያለ ነው ያ ደግ ሰው የተለያየ ሥራ የሚሰሩ ሰዎችን የሚጠይቀው፡፡ በ‘ያ ደግ ሰው የሚጠየቁ እነዚህ ሰዎች ህይወትን ከሌላ አውታር ያሳዩናል፡፡ ከኑረታቸውና ከስራቸው ሁኔታ ጋር ተነስተው ስለ ህይወት ብዙ ያወጉናል፡፡ ‘ለካስ እንዲህም አለ?!’፤ ‘ለካስ በዚህም በኩል መንገድ አለ?!’ እንድንል የሚያደርጉ ሃሳቦችን ያንሸራሽራሉ፡፡ በዚህም ደራሲው፣ በመምህሩና እንደ ማህበረሰብ ትኩረት በተነፈጋቸው ሰዎች መካከል በመመላለስ ጥቃቅን የሚመስሉ ጉዳዮችን አግዝፎ፤ የዘነጋናቸውን እኔነቶች ፊተኛው መስመር ላይ አምጥቶ፤ በተለያዩ ተረኮች የተጋረዱ ሃቆችን ግርዶሻቸውን ገላልጦ ያስነብበናል፡፡ የአንድ ደራሲና ድርሰት ኹነኛ ጉልበት ይህም አይደል፤ ያልታየውን በማሳየት፤ ከዕርጅና ውስጥ ወጣትነትን፣ ከመልከ ጥፉነት ውስጥ ውበትን፣ ከእንባ ሥር ሳቅን ፈልቅቆ ማውጣት፡፡
“ያ ደግ ሰው፣ ጤፍ አጭደው ክምር ከምረው፣ ከዐውድማው ላይ ከበው ወደሚጫወቱ ሰዎች ዘንድ ‘እንደምን አላችሁ?’ እያለ ተጠጋ፡፡ እነዚያ ሰዎች ቆሎ እየቆረጠሙ፣ ጠላ እየጠጡ በህይወት ትርጉም ዙሪያ እየተጫወቱ ነበር፡፡
ያ ደግ ሰው ከጎኑ የተቀመጡትን‘ ለመሆኑ እንዲያው ህይወት ምን ትመስላለች ብላችሁ ተስማማችሁ?’ አላቸው፡፡
…አንድ ገበሬ ብድግ ብሎ እንዲህ አለ፡ ‘ሕይወትማ በማወራ የተቀዳ ጠላ ነው የምትመስለው፤ የተደላደለች ስፍራ ካላገኘች ክንብል ብላ ትደፋለች። ወዲህም ሕይወት እቶን ላይ ያለች እሳት ናት፤ በውስጥ ጥደን የምናበስልባት፣ በእጅ የማንነካት፡፡ ሕይወት በሰባራ ገል የምትጫር ፍም ናት፤ እፍ ሲሏት የምትደምቅ፣ አየር ሲከለክሏት የምትጠቁር፣ ሕይወትማ ገል ላይ የተቀመጠች እሳት ነች፡፡” በማለት (በገጽ፣12) የገበሬዎችን የህይወት አተያይ ያጋራናል፡፡
ያ ደግ ሰው ግርባብ የሚያነሳቸው አንዳንድ ሃሳቦች፤ የሚጠይቃቸው አንዳንድ ጥያቄዎች በጣም ጥልቅ ናቸው፡፡ ህይወትን ጠልቆ በመረዳት ሂደት ውስጥ ተፈልቅቀው የወጡ ሃሳቦች በየተጓዘበት ያንፀባርቃል፡፡ “ያ ደግ ሰው፣ ወደ ልቡ ገብተው ያልተመለሱ የሰው ሀሳቦች የሱ እየመሰሉት ‘እኔ’ በማለት መደናገሩን ልብ አለ፡፡ ብዙ በመሰብሰቡ ሳቢያ ከልቡ ላይ ለራሱ የሚሆን ስፍራ አልነበረውም”…(ገጽ፣57)
…የሰው ልጅ ግን ከማህበረሰቡ ከሚማራቸውና ከማህበረሰቡ ወስዶ የራሱ ከሚያደርጋቸው ‘እውነቶች’ የተሻገረ እኔነት አለው ይሆን?! ግለሰቡ ገና ሲወለድ በማህበረሰቡ ዕቅፍ ውስጥ ነው የሚወድቀው፡፡ ከመወለዳችን በፊት ደግሞ ማህበረሰቡ አስቀድሞ የዘረጋቸው መዋቅሮችና የአስተሳሰብ አውታሮች አሉት፡፡ ግለሰቡ ለዓመታት እነዚህን ማህበረሰባዊ ዕውነቶች እንደ ተፈጥሯዊ ዕውነታ አድርጎ ነው የሚረዳቸው። እኔነቱን ጭምር የሚሰራው በዚህ ማህበረሰባዊ እሴቶችና አስተሳሰቦች ላይ በመመስረት ነው፡፡ ታዲያ ያ ደግ ሰው “ወደ ልቡ ገብተው ያልተመለሱ የሰው ሀሳቦች የሱ እየመሰሉት ‘እኔ’ በማለት መደናገሩ…“የዚሁ ተቀጥላ ይመስላል። ያ ደግ ሰው በእኔነትና በእኛነት መካከል ያለው ድንበር ተቀያይጦ ቢያደናግረው ነው ትልቁን የሕይወት ጥያቄ የጠየቀው።
በዚህ ድርሰት ውስጥ ጎልቶ የሚደመጠው አንዱ ድምጽ፣ የህይወት ብዝሃነትና አምሳለ-ብዙ ገጽታዎቹ ነው። ለዚህ አስረጅ ይሆነን ዘንድ ያ ደግ ሰው ጠይቆ፣ ወንድም ጋሼ ከመለሰው የሀሳብ ፍሬ እነሆ፤ “ከሙሉ ጎዳና መንገዶች ይልቅ መጋቢ መንገዶች ደስ ይላሉ። ምክንያቱም፣ ወደ ሜዳ ሆድ ውስጥ ይገባሉ፤ ወደ ተራራ ይወጣሉ፤ ወደ ሸለቆ ይዘምታሉ፡፡” ከዚህ አንጻር ልክ እንደ ወንድም ጋሼ፣ ህይወት አምሳለ-ብዙ ገጾች አሏት፤ እነዚህን ገጾቿን ገልጦ ማሳየት ለአንድ ከያኒ ዋነኛ ተግባሩ ሊሆን ይገባዋል፡፡
በዚህ ድርሰት ውስጥ የሚስተዋለው አንድ ጉዳይ የደራሲው ጥልቅ አስተዋይነት ነው፡፡ ደራሲው በነገሮች ላይ ጥልቅ መረዳትና አስተውሎት አለው፡፡ አብረውን የሚኖሩ ደቂቅ ፍጥረታትን በባህርያቸው ውስጥ ሰርጾ በመግባት ሲያብራራ በጣም ያስደንቃል። ሥለ ራሳችን፣ ስለ አካላችን…እንኳን ያለን መረዳት ምን ያህል ነው? በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን የምናልፍ የምናገድምባቸውን ሥፍራዎች ምን ያህል አስተውለናቸው ይሆን?… እስኪ ራሳችንን እንጠይቅ፡፡ ደራሲው ግን ከሰዎችም አልፎ የደቂቅ ነፍሳትና እንስሳት መገለጫ ባህርያቸውን ሲተነትን ያስገርማል፡፡ ይህን ለማድረግ ትልቅ አስተዋይነት ይጠይቃል፡፡
ግርባብን ስናነብበው ከኪናዊ ሥነ ጽሑፍነቱ ይልቅ ፍልስፍናዊ እሳቤዎቹ ናቸው ጎልተው የሚወጡት፡፡ እዚህ’ጋ ፍልስፍና ስል የእያንዳንዱ ገጸ-ባህሪያት የህይወት አተያይ፣ አስተውሎት ከስራቸው ሁኔታ በመነሳት ህይወትን እንዴት እንደሚገነዘቧት ለማመልከት ነው፡፡
‘ያ ደግ ሰው ግርባብ’ እንደ አንድ ኪናዊ የፈጠራ ድርሰት ጥቂት ህፀጾች አያጡትም፡፡ ከያኒው እንደ ማናችንም ሰው በመሆኑ ከድርሰቱ ምሉዕነት መጠበቅ አግባብ አይደለም፡፡ ከዚህ ቀጥሎ የተጠቀሱት ጥቂት ህፀጾችን ያነሳነው ድርሰቱን በተወሰነ መልኩ አደብዝዘውታል፤ ኪናዊ ለዛውንም ትንሽ እንዲለዝዝ አድርገውታል በሚል መነሻ ነው፡፡
ምንም እንኳን ያ ደግ ሰው ትኩረት የነፈግናቸውን ግለሰቦችና እሴቶች አጉልቶ ቢያሳየንም፤ በሌላ በኩል ደግሞ የማህበረሰቡን ዕሳቤዎች፣ እምነቶችና እሴቶች መልሶ መላልሶ የሚያስተጋባ ወይም የሚያፀና አይነት ገጸ-ባህሪ ነው። ያ ደግ ሰው ግርባብ፣ ማህበረሰቡን ግልጥልጥ አድርጎ ሲሄስ ብዙም አናየውም። ማህበራዊ እውነቶችን ለማጽናት የሚተጋውን ያህል ማህበረሰባዊ ህፀጾችን ለመተቸት ፈራ ተባ ይላል፡፡ ሌሎች ገጸ-ባህርያትም በአንድም ሆነ በሌላ የዚህን የህይወት እሳቤ የሚያስተጋቡ ናቸው፡፡
እውቁ የሥነ ጽሑፍ መምህር ዶክተር ዮናስ አድማሱ፣ “ሀዲስ አለማዬሁና የማህበራዊ ሂስ ስልታቸው” በተሰኘው ጥናታቸው፣ “የከያኒው ክሂልና ብቃት የሚመጠነው በግለሰቦች ውስጣዊ ሁኔታ ዘልቆ የማህበረሰቡን ሥነ-ልቦናዊ አሻራ እንደ ካርታ ሊያስነብበን በመቻሉ ልክ ነው” በማለት፤ የከያኒውን የሃሳብ አድማስ ከየት ወዴት ድረስ እንደሚዘረጋ ነው የሚያስገነዝቡን፡፡ ደራሲው ከየትኛውም አይነት ወገንተኝነት ተላቅቆ የማህበረሰቡን ህፀጽ እንደ ካርታ ሊያስነብበን ይገባል፤ የመምህሩ መልዕክት፡፡ በዚህ አኳኋን በ’ያ ደግ ሰው ግርባብ’ ድርሰት ውስጥ ማህበራዊ ህፀጾችን በሚታይና በሚጨበጥ መልኩ ሊያሳየን አለመድፈሩ የድርሰቱ ዋነኛ ህፀጽ ነው፡፡
ግርባብ ላይ የሚስተዋለው ሌላኛው ህፀጽ ለድርሰቱ ኪናዊ ለዛ የተሰጠው ትኩረት አንሶ መታየቱ ነው፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው የድርሰቱ የሃሳብ ትባትና ሃሳቡን ለማንሸራሸር የመረጠው ስልት የሚደንቅ ነው፡፡ ቋንቋውም ያልቸከና በጣም ውብ የሚባል ነው። ነገር ግን የማዋዛት፣ ምናብ ላይ ምስሎችን የመከሰት፣ ከገጽ ገጽ ስንሸጋገር የገጸ-ባህሪያቱ ተረኮች በቀላሉ ተገማች መሆን፣…የድርሰቱን ኪናዊ ለዛ አሳንሶታል፡፡ ግርባብ ከኪናዊ ሥነ ጽሑፍነቱ ይልቅ ወደ ፍልስፍና ይበልጥ ያጋደለ ነው የምለው አንድም ለዚህ ነው።
‘ያ ደግ ሰው ግርባብ’ ግን ሊነበብ የሚገባው ድርሰት ነው፡፡ ራሳችንን መልሰን እንድናይ፤ ማህበረሰባችንን ዘልቀን እንድንረዳ የሚያስችል ጥሩ ድርሰት ነው፡፡ ደግሞም እንደ ግርባብ ያሉ በይዘታቸውና በአቀራረባቸው ለየት ያሉ የፈጠራ ሥራዎች ለዚህ ዘመን ያስፈልጋሉ፡፡
በአብርሃም ገብሬ