
AMN – ኅዳር 10/2017 ዓ.ም
ጠንካራ ተቋማትን በመፍጠር፣ ቴክኖሎጂን በማበልፀግ፣ ጠንካራ የስራ ባህልን በመገንባት እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ በመጠቀም መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ማምጣት እንደሚቻል የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለውጦች ዙሪያ የፋይናንስ ተቋማትና የግሉ ዘርፍን ያሳተፈ ምክክር እየተደረገ ይገኛል።
በምክክሩ ላይ የተገኙት ዶ/ር ፍፁም፣ ባለፉት 60 ዓመታት የነበረውን የኢኮኖሚ ስርዓትና የመንግስትን ሚናን በተመለከተ ገለፃ አድርገዋል።
በገለፃቸውም በእነዚህ ዓመታት አገራዊ ዕድገት የተመዘገበና የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ የጨመረ ቢሆንም የኢኮኖሚ ፖሊሲው በቴክኖሎጂ ያልተደገፈ፣ የግሉን ዘርፍ ድርሻ የዘነጋና በአግባቡ የተመራ ባለመሆኑ የኢኮኖሚ ዕድገቱ አዝጋሚ እንዲሆን አድርጓል ብለዋል።
ነገር ግን ባለፉት 6 ዓመታት መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ለማምጣት በተደረገ ጥረት ኪሳራ ውስጥ የነበሩ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ትርፋማ እንዲሆኑ፣ የገቢ አቅም ብሎም የወጪ ንግድ አፈፃፀም እንዲያድግ አስችሏልም ነው ያሉት ሚኒስትሯ።
ዓለም አቀፍ የጂኦ ፖለቲካ ውጥረትና የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተፅዕኖ እያለም ቢሆን ባለፉት 6 ዓመታት አገሪቱ የነበረባትን 10 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ መክፈል ችላለች ያሉት ሚኒስትሯ በባንኮች ያለው የተቀማጭ ገንዘብ ከ700 ቢሊዮን ብር ወደ 2 ነጥብ 6 ትሪሊዮን ብር ማደጉንም አመልክተዋል።
የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፣የግብርና ምርታማነት፣ የቱሪዝም መስህብ ልማትና ዕድገት የመዋቅራዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያው ካስገኛቸው ሌሎች ስኬቶች ውስጥ ተጠቅሰዋል።
በትዕግስት መንግስቱ