ወይዘሮ ፀዳለ ሃይሌን በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የ6 ዓመት ህፃን ልጃቸውን ፋሲካ አዳነን ሲያሳክሙ ነበር ያገኘናቸው፡፡ “ልጄ በተደጋጋሚ ያፍነዋል፣ ያንኮራፋል፣ አልጋው ላይ መገለባበጥ የመሳሰሉት ምልክቶች ይታዩበት ነበር፡፡ በዚህም በጣም ከመጨነቄ የተነሳ እንቅልፍ የለኝም፤ ሳልተኛ አቅፌው ቁጭ ብዬ አድራለሁ” ሲሉ ምን ያህል የልጃቸው ህመም ያሳስባቸው እንደነበር ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል፡፡
እንደ ወይዘሮዋ ገለጻ፣ ህጻኑ ከላይ ከተጠቀሱት ምልክቶች በተጨማሪ ጉንፋን ሲይዘው ጉሮሮ አካባቢ ያብጣል፣ ለመተንፈስ በጣም ይቸገራል፣ ትንፋሹም ቁርጥ ቁርጥ ይላል፡፡ ህመሙ ሲነሳ ጨው በሞቀ ውሃ በማፍላት እየተጉመጠመጠ እንዲተፋው በማድረግ፣ ትኩስ ነገሮችን፤ ወተት እና ሻይ የመሳሰሉትን በመስጠት መታፈኑ እንዲቀንስ ጥረት ያደርጉ ነበር። እነዚህ ነገሮች አድርገው ማፈኑንም ሳይተወው፣ የእብጠት መጠኑም ሳይቀንስ ሲመጣ፣ ወደ ጤና ጣቢያ ወስደውት ምርመራ ሲደረግለት የቶንሲል ህመም እንደሆነና ስጋ የሚመስለው የተለጠፈው ነገር መውጣት እንዳለበት እንደነገሯቸው ያስረዳሉ።
“ለሁለት ዓመታት ያህል ሲያሰቃየው ለቆየው ህመም መፍትሄ ፍለጋ ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ከአንገት በላይ ህክምና ክፍል ወሰድኩት” የሚሉት ወይዘሮዋ፣ ምርመራ ተደርጎለት የቶንሲል ህመም እንደሆነና ያበጠው ካልወጣ ኢንፌክሽን በመፍጠር ተጓዳኝ ጉዳቶችን እንደሚያመጣ ተነግሯቸው በቀዶ ህክምና እንዲወጣለት መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ቀዶ ህክምናው ከተደረገለት አንድ ሳምንት የሆነው ህፃን ፋሲካ ከእናቱም አንደበት እንደሰማነው፤ እኛም እንደተመለከትነው በጥሩ የጤንነት ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ እንደልቡ ይተነፍሳል፤ እንቅልፍ ይተኛል እንዲሁም በአግባቡ ምግብ ይመገባል፡፡ “ልጆቻችን ሲታመሙ በቤት ውስጥ የምናደርጋቸው ነገሮች እንዳሉ ሆነው ከዛሬ ነገ ይሻላቸዋል በማለት ህመማቸው እንዲባባስ ማድረግ የለብንም፡፡ ወደ ህክምና ቦታ በመውሰድ በጤና ባለሙያዎች እንዲታዩ ማድረግ አለብን። የእኔ ልጅ የቶንሲሉን ማበጥ የጤና ባለሙያው ሲያሳየኝ በጣም ነው የደነገጥኩት፤ በዚህ ልክ መታመሙን አልተረዳሁለትም ነበር” ሲሉ ወደ ሀኪም ቤት መውሰድ ተገቢ መሆኑን ከራሳቸው ተሞክሮ በመነሳት መክረዋል፡፡
በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ከአንገት በላይ ስፔሻሊስት ዶክተር ኦሊያድ ታረቀኝ ለዝግጅት ክፍላችን በህፃናት ላይ ስለሚከሰተው የቶንሲል ህመም በሰጡን ማብራሪያ፣ ቶንሲል ማለት በጉሮሮ አካባቢ በምላስ ጀርባ እንዲሁም በአፍንጫ በስተጀርባ በኩል ያለው አካል ነው፡፡ ቶንሲል ደግሞ እነዚህን አካላት የሚያጠቃ ህመም ነው፡፡
የቶንሲል ህመም ሲከሰት የተለያዩ ምክንያቶች ይታያሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የመጀመሪያው በቫይረስ ምክንያት የሚመጣ ኢንፌክሽን ሲሆን፤ የላይኛውን የአየር ቧንቧ ያጠቃልላል። ይህም የተለመደና ብዙ ጊዜ የሚከሰት ነው። ሁለተኛው ደግሞ በባክቴሪያ በሚመጣ ኢንፌክሽን የሚከሰት ነው፡፡
አንድ ህፃን በቶንሲል ህመም በሚጠቃበት ወቅት የሚያሳያቸው የተለያዩ ምልክቶች አሉ፡፡ እነዚህም ምልክቶች እንደየ መንስኤዎቻቸው ይለያያሉ፡፡ ይህም በቫይረስ ኢንፌክሽን ምክንያት የተከሰተ የቶንሲል ህመም ከሆነ የሚያሳያቸው ምልክቶች ቀለል ያሉና ለጉዳትም የማይሰጡ ናቸው፡፡ መጠነኛ የሆነ የሰውነት ትኩሳት መጨመር፣ ጉሮሮ አካባቢ የመከርከርና የህመም ስሜት መሰማት እንዲሁም አጠቃላይ የሰውነት አካልን ብርድ ብርድ ማለትና መቆረጣጠም የመሳሰሉት ናቸው፡፡
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የቫይረስ ኢንፌክሽን ሆኖ ይጀምርና ባክቴሪያ ይጨመርበታል፡፡ ይህ ሲሆን በባክቴሪያ ኢንፌክሽን የሚመጣ የቶንሲል ህመም ይባላል፡፡ በዚህ ጊዜ የሚታዩ ምልክቶች ደግሞ ከፍ ያሉ ይሆናሉ፡፡ እነዚህም ከፍተኛ የሆነ ትኩሳት፣ በቶንሲል አካባቢ ያለው ህመም ለመዋጥ የሚያስቸግር መሆን፣ ምግብ መከልከልና ቶንሲሎቹ አብጠው አሊያም መግል ይዘው መታየት የመሳሰሉት ናቸው፡፡
ሌላኛው በህፃናቱ አፍንጫ ጀርባ ላይ የቶንሲል ኢንፌክሽን በሚኖርበት ወቅት የሚያሳያቸው ምልክቶች የአፍንጫ መታፈን፣ የትንፋሽ ማጠር፣ በሚተኙበት ጊዜ ማንኮራፋት፣ ልጆች በአፍንጫቸው መተንፈስ ሲከብዳቸው ከእንቅልፋቸው መባነን፣ በተኙበት አልጋ ላይ መወራጨት፣ መገለባበጥ የመሳሰሉት ምልክቶች ሊታዩባቸው ይችላል፡፡
ለህመሙ የሚደረግ ህክምና በቤት ውስጥ የሚደረገው የመጀመሪያ የህክምና እርዳታ ሲሆን፤ ይህም በቫይረስ ምክንያት ለሚከሰተው የቶንሲል ህመም ተመራጭና የሚመከር ነው፡፡ በቤት ውስጥ ማከም እየተቻለ ወደ ህክምና ቦታ መውሰዱም ምንም የተለየ ነገር አያስገኝም፡፡ ሰውነታቸው በጣም ሲተኩስ በቀዝቃዛ ጨርቅ ለማቀዝቀዝ መሞከር እንዲሁም በውስጣቸው ቫይታሚን ሲ ያላቸው ምግቦች እንደ ብርቱካን፣ እንጆሪ፣ ቃሪያ፣ ጎመንና የመሳሰሉትን አትክልትና ፍራፍሬ አብዝቶ መስጠት፣ ፈሳሽ ነገሮችን በሻይ ወይም በወተት መልክ እንዲወስዱ በማድረግ በቤት ውስጥ ማከም ተገቢ እንደሆነ ዶክተር ኦሊያድ ያስረዳሉ፡፡
እነዚህ የቤት ውስጥ ህክምናዎች ተደርገው ትኩሳቱ የማይቀንስ ከሆነ፣ የህፃኑ የንቃተ ህሊና እየቀነሰ ከሄደ፣ ድካምና የመዛል ስሜት ካሳየ፣ ወደ ህክምና ተቋማት መውሰድ አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህም የባክቴሪያ ኢንፌክሽን ያመጣውን ትኩሳት በቤት ውስጥ ማከም ስለሚያስቸግር ትኩሳቱን የሚያስታግስ መድሃኒት ይሰጠዋል፡፡ ቶንሲሉ ያለበት ቦታ የአፍንጫ ጀርባ ወይስ የጉሮሮ ተብሎ ይታይና በባክቴሪያ ምክንያት የተከሰተ የቶንሲል ኢንፌክሽን ከሆነ ፀረ ባክቴሪያ መድሃኒቶች ይታዘዝለታል፡፡
ሌላኛው ህክምና አንድ ህፃን ልጅ በአንድ ዓመት ሰባት ጊዜ እና ከዚያ በላይ፣ በሁለት ተከታታይ ዓመታት አምስት ጊዜና ከዚያ በላይ እንዲሁም በሶስት ተከታታይ ዓመታት ሶስት ጊዜና ከዚያ በላይ ካመመው በባክቴሪያ የሚመጣ የቶንሲል ኢንፌክሽን የሚባለው ደረጃ ላይ ይደርሳል ይላሉ ዶክተር ኦሊያድ፡፡
በተጨማሪም ከጉሮሮ ቶንሲል ውጭ የአፍንጫ እብጠት እንዳለው ከተለየ፣ የእብጠት ደረጃው ተለይቶ ህፃኑ በትንፋሽ ማጠር ምክንያት በአንድ ሌሊት ከሶስት ጊዜ በላይ የሚባንን፣ ትምህርት የመቀበል አቅሙ ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር ሲነፃፀር ዝቅ ያለ፣ ክብደቱ እየቀነሰ ከሄደ የአፍንጫ ጀርባ የቶንሲል ህመም መያዙን የሚያሳይ ሲሆን በቀዶ ህክምናም እንዲወጣ ይደረጋል፡፡
መጠነኛ የሆነ ማንኮራፋትና አልፎ አልፎ ጉንፋን በሚይዘው ጊዜ እና የአየር ፀባዩ በሚቀያየርበት ወቅት ብቻ የሚባባስ ከሆነ ደግሞ በሽሮፕ መልክ በአፍንጫ በኩል በሚሰጡ መድሃኒቶች ማከምም ይቻላል፡፡
በባክቴሪያ ኢንፌክሽን የሚመጣው የቶንሲል ህመም በወቅቱ ካልታከመ የልብ ችግር እና የኩላሊት የማጣራት አቅምን ወይም ህዋሳትን እንደሚጎዳ የሚናገሩት ዶ/ር ኦሊያድ፤ በቤት ውስጥ ከሚደረገው ህክምና በተጨማሪ ወደ ህክምና ተቋማትም መውሰድ ተገቢ መሆኑን ይመክራሉ፡፡
አብዛኛውን ጊዜ በህፃናት ላይ የሚከሰት የቶንሲል ህመም በትንፋሽ የሚተላለፍ የጉሮሮና የአፍንጫ ጀርባ ህመም በመሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ በተለይ ትምህርት ቤት አካባቢ ቶንሲል የታመመ ልጅ ካለ ህክምና አግኝቶ እስኪሻለው ድረስ ቤት ውስጥ እረፍት እንዲያደርግ ይመከራል፡፡
ዶክተር ኦሊያድ እንደነገሩን በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ በየቀኑና በየሳምንቱ የሚታከሙ ህፃናት ቁጥር በውል ተለይቶ ባይታወቅም ከበፊቱ ጋር ሲነፃፀር ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በዲፓርትመንቱም ቁጥር አንድ ላይ የሚቀመጥ ነው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት የማህበረሰቡ መረጃ የማግኘት ንቃተ ህሊና መጨመርና ወደ ህክምና ተቋማት ማምጣት እያደገ ከመምጣቱ ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል፡፡
የቶንሲል ህመም በአብዛኛው በህፃናት ላይ የሚከሰት ነው፡፡ ይህ ህመም ሲከሰት ግን መጀመሪያ በቤት ውስጥ ህክምና መንከባከብ ተገቢ ነው፡፡ እንክብካቤ ተደርጎላቸውም ለውጥ የማያመጡና የቶንሲል ህመሙ ተደጋግሞ የሚከሰት ከሆነ ለሌሎች ተጓዳኝ ህመሞች እንዳይዳርግ ለህክምና ባለሙያዎች ማሳየትና ተገቢውን ህክምና እንዲያገኝ ማድረግ አስፈላጊ ነው ሲሉም ዶክተር ኦሊያድ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡
በፋንታነሽ ተፈራ