AMN-ጥር 8 /2017 ዓ.ም
በዛሬው ዕለት በፖሊስ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት 3 ባለሙያዎች የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አነስተኛ ግብር ከፋዮች የደረሰኝ ቁጥጥር ባለሙያዎች ናቸው ።
የቅርንጫፍ ፅ/ቤቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሙሉ ኃይለሚካሄል እንደገለፁት በቁጥጥር ስር የዋሉት 3 የደረሰኝ ቁጥጥር ባለሙያዎች በወረዳ 7 አውቶቡስ ተራ አካባቢ ከቶፕ ውሃ ሽያጭ ባለሙያ በደረሰኝ ቁጥጥር 5 ሺህ ብር ጉቦ መቀበላቸው በአካባቢው ድርጊቱን ሲታዘቡ የነበሩ ሰዎች ባደረሰው ጥቆማ ነው።
ፖሊስ ከግለሰቦቹ በደረሰው ጥቆማ መሰረትም ከቁጥጥር ባለሙያዎቹ አስተባባሪ ቦርሳ በፍተሻ የተቀበሉት 5 ሺህ ብር በማግኘቱ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ አድርጓል ብለዋል ።
በአሁኑ ወቅትም ተጠርጣሪዎቹ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑ ለማወቅ ተችሏል።
በተመሳሳይ የመርካቶ ቁጥር 1 መካከለኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ፅ/ቤት የታክስ ኦዲተር የሆነ ግለሰብ የ150 ሺህ ብር ጉቦ በመቀበሉ በቁጥጥር ስር ውሏል።
ተጠርጣሪው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ሊውል የቻለው የፌዴራል ወንጀል ምርመራ በደረሰው ጥቆማ መሰረት በተደረገ ክትትል ሲሆን ግብር ከፋዩ ለመንግስት መክፈል ያለበትን ግብር ለመቀነስ በመስማማት ከጠየቀው 150 ሺህ ብር 100 ሺህ ብሩ በቼክ መቀበሉም ተረጋግጧል።
ይሁንና ቀሪውን 50 ሺህ ብር በጥሬ ገንዘብ ሲቀበል እጅ ከፍንጅ ተይዞ በአሁኑ ወቅት ጉዳዩ በህግ እየታየ መሆኑን ከአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።