ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላምና ልማት ትስስር የመፍጠር ጥረቷ የሚደነቅ ነው- የተርኪዬ ኤኬ ፓርቲ ምክትል ሊቀ መንበር ዛፈር ሲራካያ

You are currently viewing ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላምና ልማት ትስስር የመፍጠር ጥረቷ የሚደነቅ ነው- የተርኪዬ ኤኬ ፓርቲ ምክትል ሊቀ መንበር ዛፈር ሲራካያ

AMN – ጥር 22/2017 ዓ.ም

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የልማት ትስስር እና ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር የምታደርገው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን የተርኪዬ ጀስቲስ ኤንድ ዴቨሎፕመንት (ኤኬ) ፓርቲ ምክትል ሊቀ መንበር ዛፈር ሲራካያ ገለጹ።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ብልጽግና ፓርቲ ለዓመታት ለዘለቀውና በሁኔታዎች ለማይለዋወጠው የኢትዮጵያ እና ተርኪዬ ወዳጅነት እውቅና እንደሚሰጠውም ገልጸዋል።

“ከቃል እስከ ባህል” በሚል መሪ ሀሳብ ከጥር 23 እስከ 25 ቀን 2017 ዓ.ም በሚያካሄደው የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባኤ የሚሳተፉ የተለያዩ ሀገራት እህት ፓርቲ ተወካዮች አዲስ አበባ በመግባት ላይ ይገኛሉ።

በዚህም የተርኪዬ ኤኬ ፓርቲ ምክትል ሊቀ መንበር ዛፈር ሲራካያን የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ የተርኪዬ ኤኬ ፓርቲ ምክትል ሊቀ መንበር ዛፈር ሲራካያን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ከውይይቱ በተጨማሪ በኢትዮጵያና ተርኪዬ መካከል በተለያዩ መስኮች ያለውን ትብብር ለማጠናከር በመርሆች ላይ የተመሰረተ የጋራ መድረክ ለመፍጠር በብልጽግና እና ኤኬ ፓርቲዎች መካከል የመግባቢያ ስምምነት ተፈርሟል፡፡

የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ እና የተርኪዬ ኤኬ ፓርቲ ምክትል ሊቀ መንበር ዛፈር ሲራካያን ስምምነቱን ፈርመውታል፡፡

የመግባቢያ ስምምነቱ የጋራ ፖለቲካዊ ትብብር ለመፍጠር በመሪዎች ደረጃ ግንኙነት መመስረትና ሀሳብ ለመለዋወጥ፣ የትምህርትና አቅም ግንባታ፣ የሴቶችና ወጣቶችን የጋራ የሁለትዮሽ መድረክ ማዘጋጀትን ያካተተ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል የጋራ ተጠቃሚነትን ያማከለ በጤና፣ ግብርና ባህልና ቱሪዝም ዘርፎች የንግድና ምጣኔ ሀብት ትስስር መፍጠር የሚያስል ነው ተብሏል፡፡

የተርኪዬ ኤኬ ፓርቲ ምክትል ሊቀ መንበር ዛፈር ሲራካያ፤ ኢትዮጵያ እና ተርኪዬ በመተባበር ላይ የተመሰረተ የረጅም ጊዜ ወዳጅነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ካሉ ሀገራት ግንባር ቀደሟ የተርኪዬ አጋር መሆኗን ጠቅሰው፤ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የተርኪዬ ፕሬዝዳንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶጋን በኢትዮጵያና ሶማሊያ መካከል የነበረውን አለመግባባት እንዲፈታ በትኩረት መስራታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የምስራቅ አፍሪካ ወሳኝ ወንድማማች ሀገራት መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ትብብራቸውም ይበልጥ የሚጠናከርበት ሁኔታ መፈጠሩን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የልማት ትስስርን ለማጠናከርና ሰላምና መረጋጋትን ለመፍጠር የምታደርገውን ጥረት አድንቀው ተርኪዬ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት የምታደርገውን እገዛና ድጋፍ አጠናክራ የምትቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ፤ ብልፅግና ለዓመታት ለዘለቀውና በሁኔታዎች ለማይለዋወጠው የኢትዮጵያ እና ተርኪዬ ወዳጅነት እውቅና ይሰጣል ብለዋል።

የተርኪዬ መንግሥት እና ፕሬዝዳንት ሬሴብ ጣይብ ኤርዶጋን በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የተከሰተውን አለመግባባት በውይይት እንዲፈታ ስላደረጉት ጥረትም ምስጋና አቅርበዋል።

ብልጽግና ፓርቲ እና ኤኬ ፓርቲዎች አካታች የህዝብ አስተዳደርና ልማት እንዲሰፍን የሚሰሩ በመሆናቸው ትብብራቸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ በግብርና በተለይም በስንዴ፣ ሩዝ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በራስ አቅም በማምረት ራሷን መቻሏን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የምንዛሪ ተመኑን በማረጋጋት የውጭ ኢንቨስተሮችን እየሳበ መሆኑን በመጠቆም፣ የተርኪዬ ባለሀብቶች በስፋት እየተሳተፉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review