በብራዚል የሚካሄደው 30ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ 30) የተገቡ ቃሎች ወደ ተግባር የሚቀየሩበት ወሳኝ ምዕራፍ ሊሆን እንደሚገባ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ።
የ2025 የፒተርስበርግ የአየር ንብረት ለውጥ ምክክር በጀርመን በርሊን ከተማ ዛሬ መካሄድ ጀምሯል።
ውይይቱን ያዘጋጁት የጀርመን እና ብራዚል መንግስታት በጋራ በመሆን ነው።
የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በውይይቱ ላይ እንዳሉት ኢትዮጵያ የፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ግቦች ሁሉን አቀፍ መገምገሚያ ማዕቀፍ (1st Global Stocktake) የመጀመሪያ ምዕራፍ የተቀመጡ ምክረ ሀሳቦችን ለሙሉ ለሙሉ ለመተግበር በቁርጠኝነት ትሰራለች።
አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተጽእኖዎች ለመግታት በአዲስ መልክ የጋራ ቁርጠኝነት በማደስ አበክሮ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ እ.አ.አ ሴፕቴምበር ወር 2025 የሚካሄደውን ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ እንደምታሰናዳና ይህም ለአየር ንብረት ለውጥ እርምጃዎች ያለውን ዘላቂ ቁርጠኝነት እና የአመራር ሰጪነት ሚና በግልጽ የሚያመላክት መሆኑን ተናግረዋል።
ሚኒስትሯ ኢትዮጵያ በብራዚል የሚካሄደው 30ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ 30) የተገቡ ቃሎች ወደ ተግባር በመቀየር ያለፈውን ታሪካችንን በማረም በትክክለኛው ጎዳና ለመጓዝ ወሳኝ የሽግግር ነጥብ እንዲሆን ጥሪ ታቀርባለች ብለዋል።
ኮፕ 30 እ.አ.አ በኖቬምበር ወር 2025 በብራዚል ቤሌም ከተማ ይካሄዳል።
የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ከጉባኤው ጎን ለጎን ከኮፕ 30 ፕሬዝዳንት አንድሬ ኮሪያ ዶ ላጎ ጋር ውይይት አድርገዋል።
ውይይቱ ኢትዮጵያ እና ብራዚል በኮፕ 30 አጀንዳዎች ላይ በትብብር መስራት እና ኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ እና የምግብ ስርዓት ማሻሻያ ኢኒሼቲቮችን ጨምሮ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ስራዎቿን ለጉባዔው ተሳታፊዎች በምታቀርበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው።
ፕሬዝዳንት አንድሬ ኢትዮጵያ “United for Bio- coalition” የተሰኘውን ጥምረት እንድትቀላቀል ጋብዘዋል።
ብራዚል ኢትዮጵያ በኮፕ 29 ጉባዔ ስራዎቿን እንድታሳይ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ ቃል ገብተዋል።
በተያያዘም ሚኒስትሯ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ማዕቀፍ (ዩኤንኤፍሲሲ) ዋና ፀሐፊ ሳይመን ስቲል ጋር ተወያይተዋል።
ሁለቱ ወገኖች ለአየር ንብረት ለውጥ ፈተናዎች መፍትሄ ማበጀት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በቅርበት ለመስራት ተስማምተዋል።
ሚኒስትሯ ለዋና ጸሐፊው እና ለፕሬዝዳንቱ ኢትዮጵያ በምታዘጋጀው አህጉራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ላይ እንዲሳተፉ ጋብዘዋል።
የ2025 የፒተርስበርግ የአየር ንብረት ለውጥ ምክክር እስከ ነገ እንደሚቆይ የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ምክክሩ በየዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን ዘንድሮ የኮፕ 30 ተፈላጊ ውጤቶች ላይ ጉልህ ተጽእኖ ማሳረፍ የሚችሉ የዓለም 40 ሀገራት ተወካዮች መገኘታቸው ተገልጿል።