AMN- ጥቅምት 15/2017 ዓ.ም
16ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ የኢትዮጵያን ተደማጭነትን ከፍ ያደረገ እና ትልቅ የዲፕሎማሲ ውጤት የተገኘበት ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
በሩሲያ ካዛን በተካሄደው በዚህ ጉባኤ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ልዑካን ቡድናቸው ተሳትፈዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በጉባኤው የኢትዮጵያን ተሳትፎ አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በጉባዔው ላይ የተለያዩ አጀንዳዎች መነሳታቸውን ያመለከቱት ሚኒስትሩ በውይይቱ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ውጤታማ እንደነበር አንስተዋል፡፡
በጉባኤው የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስከብሩ ሀሳቦች መንሸራሸራቸውን እና በዚህም ተሰሚነቷ ከፍ ያለበት ውጤታማ የዲፕሎማሲ ስራ መከናወኑን አስረድተዋል፡፡
በአባል አገራቱ መካከል ኢኮኖሚዊ ትብብሮች፣ የአካባቢ ጥበቃ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ማሻሻያን የተመለከቱ ውሳኔዎች ተላልፈዋል ሰሉም ገልጸዋል፡፡
በጉባኤው የተላለፉ ውሳኔዎችን አስመልክቶ ኢትዮጵያ አቋሟን ማንጸባረቋንም አንስተዋል፡፡
ከጉባዔው ጎን ለጎን ከተለያዩ አገራት መሪዎች ጋር ውጤታማ ውይይቶች መደረጋቸውን ያወሱት ሚኒስትሩ በሁለትዮሽ ውይይቶቹ ላይ መሪዎቹ ኢትዮጵያ በቀጣናው እና በአፍሪካ ያላትን አቋም እና ብሄራዊ ጥቅሞቿን በተመለከተ ግንዛቤ ማግኘታቸውን አስረድተዋል።
በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የሩሲያው ፕሬዝዳን ቭላድሚር ፑቲን ጥልቅ እና ውጤታማ የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውን አመልክተዋል፡፡
ሁለቱ አገራት ትብብራቸውን ይበልጥ ማጠናከር በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።
በቀጣይ ተቀራርበው በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይም ከመግባባት ላይ መድረሳቸውን ሚኒስትሩ አመልክተዋል፡፡
አገራቱ የቆየ ታሪካዊ ወዳጅነት እና ትብብር እንዳላቸው የተናገሩት ሚኒስትሩ በተለያዩ መስኮች ላይ የሁለትዮሽ ስምምነቶች ማድረጋቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
በጉባዔው ላይ ከአባል አገራቱ በተጨማሪ ከብሪክስ ጋር በአጋርነት መስራት የሚፈልጉ አገራት መሳተፋቸውንም ገልጸዋል፡፡
በሰለሞን በቀለ