
AMN-ግንቦት 10/2017 ዓ.ም
በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 37ኛ ሳምንት መርሃግብር ዛሬ አምስት ጨዋታዎች ይከናወናሉ።
አርሰናል በኤምሬትስ ኒውካስትል ዩናይትድን ያስተናግዳል። ምሽት 12፡30 የሚጀምረው ጨዋታ ለሁለቱም ክለቡች ወሳኝ ነው፡፡ አርሰናል 68 ኒውካስትል ዩናይትደ 66 ነጥብ ሰብስበው ሁለት እና ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡
መድፈኞቹ ዛሬ ድል ከቀናቸው የቻምፒየንስ ሊግ ተሳታፊነታቸውን ያረጋግጣሉ፡፡ ከኒውካስትል ዩናይትድ የሚጠብቃቸው ፈተና ግን ቀላል አይሆንም፡፡አርሰናል በውድድር ዓመቱ በካራባኦ ካፕ እና በሊጉ በሦስት ጨዋታዎች በኒውካስትል ተሸንፏል፡፡

በቀጣይ ዓመት አዲስ ወዳስገነባው ስታዲየም የሚያቀናው ኤቨርተን የመጨረሻ የጉዲሰን ፓርክ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል፡፡ 8 ሰዓት ላይ ከሳውዛምፕተን ጋር በሚያደርገው በዚህ ጨዋታ 132 ዓመት የተጠቀመበትን ስታዲየሙን ብቻ ሳይሆን አሽሊ ያንግን ጨምሮ በክለቡ የማይቆዩ ተጫዋቾችንም ያሰናብታል፡፡
ሰሞነኛ ብቃቱ ጥሩ ያልሆነው ኖቲንግሃም ፎረስት ወደ ለንደን አቅንቶ ዌስትሃም ዩናይትድን ይገጥማል፡፡ የቻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎን ለማግኘት አሁንም እድል ያላቸው ፎረስቶች በ62 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ ጨዋታው 10፡15 ላይ ይጀምራል፡፡
11 ሰዓት ላይ ብሬንት ፎርድ ከ ፉልሃም ፤ ሌስተር ሲቲ ከ ኢፕስዊች ታውን የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች የዛሬ መርሃግብር አካል ናቸው፡፡
በሸዋንግዛው ግርማ