ኦሮሚያ ባንክ ያለምንም የዋስትና ማስያዣ ብድር መስጠት የሚያስችል ”ሚልኪ” የተሰኘ አዲስ የዲጂታል የብድር አገልግሎት መተግበሪያ በስራ ላይ ማዋሉን ገልጿል።
በወርሀዊ ደሞዝ ለሚተዳደሩ፣ የደሞዝ መዳረሻ ብድርን ጨምሮ የብድር አቅርቦት አስፈልጓቸው በዋስትና ማስያዣ ምክንያት አገልግሎት ላጡ ዜጎች ያለምንም ዋስትና ብድር የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸቱን ነው ባንኩ ያስታወቀው፡፡
ኦሮሚያ ባንክ ይህን አገልግሎት የሚያቀርበው ከኳንተም ቴክኖሎጂ አክስዮን ማህበር ጋር በመሆን ባበለፀገው “ሚልኪ” የተሰኘ የዲጂታል የብድር አገልግሎት መተግበሪያ አማካኝነት ነው።
መተግበሪያው በቀላል መልኩ ብድርን ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ ለማድረግ ያለመ የዲጂታል አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ስለመሆኑም ተነግሯል።
መተግበሪያው ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል፣ ”ሚልኪ ፉርቱ ” ለዕለት ገቢ መተዳደሪያ እና ”ሚልኪ ሀርሜ” ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የዲጂታል ብድር አገልግሎት ይገኝበታል።
ባንኩ ያለማስያዣ ዋስትና ለጥቃቅን እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች፣ ለኤለክትሮኒክስ እና ለቤት ቁሳቁስ መግዣ የሚያስችል ጥቅሎች በመተግበሪያው ማካተቱን አስታውቋል።
በዝናሽ ሞዲ እና ወንድምአገኝ አበበ