የጤና ባለሙያዎች ያሏቸዉን ጥያቄዎች እያገለገሉ የሚጠይቁት እንጂ ከሙያዊ ስነምግባር ውጪ ስራ አቁመው የሚጠይቁ አለመሆኑን አረጋግጠዋል ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ

You are currently viewing የጤና ባለሙያዎች ያሏቸዉን ጥያቄዎች እያገለገሉ የሚጠይቁት እንጂ ከሙያዊ ስነምግባር ውጪ ስራ አቁመው የሚጠይቁ አለመሆኑን አረጋግጠዋል ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ

AMN- ግንቦት 20/2017 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልዕክት፣ የላቀ የጤና አገልግሎት ለሀገር ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል በየደረጃው ሲካሄድ የነበረው የጤና ባለሙያዎች ውይይት የማጠቃለያ መድረክ አድርገናል ብለዋል።

መድረኩ የጤና ባለሙያዎች ለሀገር ግንባታ ያላቸውን ሚና በመረዳት በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ፣ ለሀገር ግንባታ በጋራ መቆምን ፣ የተሻለ አገልግሎት መስጠት በሚቻልበት መንገድ ላይ ለመምከር እና ከባለሙያዎቹ የሚነሱ ጥያቄዎችን እና ሃሳቦችን በማዳመጥ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት የተዘጋጀ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የጤና ባለሙያዎቹ በከተማዋ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች እና የተገነቡ መሰረተ ልማቶች ጤናማነቱ የተጠበቀ ማኅበረሰብን ለመፍጠር እንዲሁም በሽታዎችን ለመከላከል አጋዥ መሆናቸዉን ያነሱ ሲሆን፣ በጤና ሴክተር ላይ እየተሰራ ያለው ስራ ተስፋ ሰጪ እና የሁሉን ትብብር የሚጠይቅ መሆኑ ላይም ተግባብተናል ብለዋል።

በቀጣይ የጤና ሴክተሩን ደረጃ ይበልጥ ለማሳደግ፣ ነባር የጤና ተቋማት ለማሻሻል፣ ከተማችንን የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የተጀመሩ አዳዲስና ዘመናዊ የጤና ተቋማትን ግንባታ ማጠናቀቅ፣ ብቁ የጤና ባለሙያዎችን ማፍራት፣ ወቅቱ የደረሰበት ዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎች ማሟላት እንዲሁም የጤና ባለሙያዎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሰረታዊ ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥተን የምንሰራ ይሆናል ሲሉም ገልጸዋል::

የጤና ባለሙያዎቹ በርከት ያሉ የጥቅማጥቅም እና የደሞዝ ማሻሻያ ጥያቄዎችን እና ሃሳቦችን ያነሱ ሲሆን፣ አገልግሎትን የሚመጥን ጥቅማጥቅም አለመኖሩን በመገንዘብ እየተሰራ ባለዉ በጤና ሪፎርም ጥናት ላይ በመመስረት በአጭር ፣ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን አምነንበታል ብለዋል።

በከተማ አስተዳደሩ አቅም የሚፈቱትን የትርንስፖርት አገልግሎት ፣በማህበር ተደራጅቶ የመኖሪያ ቤት መገንባትን ፣ ነፃ የህክምና አገልግሎት፣ የትርፍ ሰዓት ክፍያን መመሪያ በተሟላ ሁኔታ መተግበርን ጨምሮ አስተዳደሩ በአጭር እና በመካከለኛ ጊዜ እቅድ ምላሽ ለመስጠት መግባባታቸውንም አመላክተዋል::

በመጨረሻም ያሏቸዉን ጥያቄዎች ቢሆን እያገለገሉ የሚጠይቁት እንጂ ከሙያዊ ስነምግባር ውጪ ስራ አቁመዉ የሚጠይቁት አለመሆኑን አረጋግጠዋል ሲሉ ገልጸዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review