ተግባር የገለጠው ሀገር ወዳድነት

You are currently viewing ተግባር የገለጠው ሀገር ወዳድነት

አቶ ጣሀ ያጅቦ ትውልድና እድገታቸው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ሰባት ቤት ጉራጌ ዞን፣ በጌታ ወረዳ ይሁን እንጂ ኑሮን ለማሸነፍ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሰዋል፡፡ አሁን ላይ ወደ ከተሙበት አዲስ አበባ የመጡትም በ2000 ዓ.ም. ነው፡፡ የተወለዱበትን አካባቢ እና ቤተሰብ ርቀው ሲሄዱ ገና የ6ኛ ክፍል ተማሪ ነበሩ፡፡ በትምህርታቸው ባይገፉበትም አሁን ላይ  እንጀራ የሚበሉበትን የእንጨት ምርቶች ሙያን የለመዱት የ11 ዓመት ልጅ እያሉ ጅማ አጋሮ  እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

አዲስ አበባ እንደመጡ ይሰሩበት የነበረው የእንጨት ምርቶች መስሪያ ድርጅት የሚሸጠውን ግብዓት በሒሳብ መመዝገቢያ ማሽን (ካሽ ሬጅስተር) ደረሰኝ ማከናወን ጀመረ፡፡ በወቅቱ እሳቸው ስለ የሒሳብ መመዝገቢያ ማሽኑ (ካሽ ሬጅስተር) ጥቅም ጠይቀው ተረዱ፡፡ በዚህ መንገድ በደረሰኝ ግብይት መፈጸም ለሀገር ልማትና ለህዝብ ጥቅም ፋይዳው የጎላ እንደሆነ ግንዛቤ ጨበጡ። ይህንን ከተረዱ በኋላ ማንኛውንም ነገር ሲገዙ ደረሰኝ መጠየቅ ጀመሩ፡፡ ምንም ነገር ያለደረሰኝ ግብይት አይፈፅሙም። ምግብ ቤት ተመግበው ያለደረሰኝ አይከፍሉም። በጊዜ ሂደት ስለግብር፣ ለሀገር ልማት ስላለው አበርክቶ ያላቸው ግንዛቤ እያደገ መጣ፡፡

ያለደረሰኝ ግብይት ካለመፈጸም ጋር ተያይዞ ያጋጥማቸው የነበረውን ችግር ሲገልጹ፤ በቀጥታ “አልሸጥም!” የሚል ባያጋጥማቸውም፤ ደረሰኝ ሲጠይቋቸው የማይደሰቱ ግለሰቦች እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡ የሚፈልጉት ነገር እያለ የለም የሚባሉበት ጊዜ እንዳለም አልደበቁም፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የማይረሱትን ገጠመኝ ፣

“ፒያሳ አካባቢ አንድ ስጋ ቤት ቁርሴን ለመብላት ገብቼ ዱለት አዘዝኩ፡፡ ሆኖም አስተናጋጆቹ ያለውን ምግብ የለም አሉኝ። የሥጋ ቤቱ አስተናጋጆች ይህን ያሉት “የለም ሲባሉ ትተው ይወጣሉ” በሚል ነበር፡፡ እኔም ጥብስ አዝዤ መመገብ ጀመርኩ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ከእኔ በኋላ ለመጡ ሰዎች የለም የተባለው ዱለት ተሰርቶላቸው ሲበሉ ተመለከትኩ። በወቅቱ ምንም ሳልናገር ወጣሁ፡፡ በሌላ ጊዜ ተመልሼ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ሰራሁ” ሲሉ አስታውሰዋል፡፡

በንግድ ሥራ ላይ ለተሠማሩ እና ደረሰኝ የመቁረጥ ችግር ወይም የግንዛቤ እጥረት ላለባቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ግንዛቤ ለመፍጠር ከሚጠቀሙባቸው መልዕክቶች መካከል፤ “በሁሉም ደረጃ ባሉ የመንግስት ትምህርት ቤቶች (ከ1ኛ ክፍል እስከ ዩኒቨርስቲ) ድረስ ልጆቻቸውን ማስተማራቸውን ከጠየቁ በኋላ ለትምህርት ቤቶቹ ግንባታና ለትምህርት ቁሳቁስ የሚወጣው አጠቃላይ ወጪ ከህዝብ ከሚሰበሰብ ግብር ነው” የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡

ይህንን ሀገራዊ አስተሳሰብ ከራሳቸው አልፎ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር አቶ ጣሀ ረጅም ርቀት ተጉዘዋል፡፡ ለ8 ዓመታት ያህል ግብይት የፈጸሙባቸውን አራት ሺህ የሚሆኑ ደረሰኞችን አጠራቅመዋል፡፡ በአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ አማካኝነት “ግብር ለሀገር!” በሚል በተዘጋጀ አንድ የሩጫ መርሀ ግብር ላይ በደረሰኝ የተሠራ ልብስ ለብሰው በመሮጥ ለህብረተሰቡ ትልቅ ግንዛቤ የሚፈጥር ማስታወቂያም ሰርተዋል። የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ “በደረሰኝ የሚገበያይና ደረሰኙንም ለሚያጠራቅም ሽልማት እሰጣለሁ” ብሎ ያሰራጨውን ማስታወቂያ ሰምተው ወደ ተቋሙ እንደሄዱና እውቅና እንዳገኙ ይናገራሉ፡፡

በወቅቱ እውቅና ከማግኘታቸውም ባለፈ ከተቀጣሪነት ወደ ቀጣሪነት ያሸጋገራቸውን ስራ በሙያቸው መስራት የሚችሉበትን የመስሪያ ቦታ እንዲሁም የብድር አገልግሎት አግኝተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአየር ጤና ቻይና ካምፕ አካባቢ፤ በእንጨት ስራ ሙያ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ ከራሳቸው አልፎም ለአምስት ወጣቶች የስራ እድል ፈጥረዋል፡፡ 

እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ እንዳልነበሩ አቶ ጣሀ ተናግረዋል፡፡ እውቅና ካገኙ በኋላ የመሥሪያና የብድር አገልግሎቱን ለማግኘት ረጅም ጊዜ በመውሰዱና የቀጠራቸው ድርጅትም በሳቸው ምትክ ሌላ ሰው በመቅጠሩ ምክንያት ሥራ ለማቆም ተገድደው ነበር፡፡ ሆኖም የተገባላቸው ቃል ተግባራዊ ሲሆን ከአጋጠማቸው ኢኮኖሚያዊ ጫና መላቀቅ፣ በጊዜ ሂደትም ተቀጥሮ ከመስራት ወደ ቀጥሮ ማሰራት መሻገር ችለዋል፡፡

ግብር ለሀገር ልማት ወሳኝ ስለመሆኑ አስረጂ አያሻውም የሚሉት አቶ ጣሀ፣ እያንዳንዱ ዜጋ ግብር የሚከፍለው በተዘዋዋሪ ራሱ ለሚጠቀምበት ልማት መሆኑን መርሳት የለበትም በማለትም ያስገነዝባሉ፡፡

ሁሉም ግብይቱን በደረሰኝ ካደረገና በቂ ግብር ከተሰበሰበ እንደ ሀገር ጥቅሙ ብዙ ነው፡፡ ሀገርን በራስ አቅም ማልማት ይቻላል፡፡ የተለያዩ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች ይበዛሉ፡፡ የእነዚህ መብዛት ደግሞ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ማስቀረት ያስችላል፡፡ ይህ ደግሞ የውጭ ምንዛሬን ያስቀራል ሲሉም አክለዋል፡፡

አቶ ጣሀ በሚያውቋቸው ሰዎች አንደበት

አቶ ጌታቸው ሀይሌ በእንጨት ስራ የተሰማሩ ባለሀብት ናቸው፡፡ አቶ ጣሀ ከ10 አመታት በላይ እሳቸው ጋር ተቀጥረው መስራታቸውን ገልጸው በአሁኑ ወቅት በረጅም ጊዜ ልምድና እውቀት የራሳቸውን የእንጨት ስራ በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ አቶ ጣሀ ስለ ግብር የተለየ ግንዛቤ እንደነበራቸውና ግብር መክፈል ለራሳችሁ ነው እያሉ ይመክሩና ያነሳሱ እንደነበር ይገልጻሉ። ሻይ እንኳን ጠጥተው ያለደረሰኝ አልከፍልም ይሉ ነበር፡፡ ግብር መከፈል አለበት በሚል ተቀጥረው የሚሰሩበትን ድርጅት ጭምር ይቆጣጠሩ ነበር፡፡ ግብር የከፈሉባቸውን ደረሰኞች በማሰባሰብ ለሚዲያዎችም ያስተዋውቁም ነበር። ለመንግስት ግብር እንዲከፈል ጥረት ያደርጉ ስለነበር ብዙዎች ካድሬ ነህ እንዴ ይሏቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

በሶፋ ንግድ የተሰማሩት ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ራህማ መሀመድ የአቶ ጣሀ የረጅም ጊዜ ደምበኛ ናቸው፡፡ ከ3 ዓመታት በላይ የሶፋ ግብይት መፈጸማቸውን በመግለጽ፣ “ይደርሳል ብሎ በሰጠው ቀጠሮ ያደርሳል፡፡ ደረሰኙንም አብሮ አዘጋጅቶ ነው የሚጠብቀው፡፡ ደረሰኝ ሳይቆረጥ የሰራውን አይሸጥም” ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

እንደ መውጫ

በደረሰኝ ግብይት መፈጸም ባህል እንዲሆን ምን መሰራት እንዳለበት በሰጡት ሃሳብ እንደጠቆሙት፤ በቅድሚያ ማህበረሰቡ ግብር መክፈሉ ጥቅሙ ለራሱ መሆኑን ማንቃት ያስፈልጋል፡፡ ግብር መክፈል ሀገር ወዳድ መሆንን የሚያሳይ ጤነኛ አስተሳሰብ እንደሆነና በተከፈለው ግብር የሚሰሩት ልማቶች ከራስ አልፈው ለልጆች እንደሚውሉ ማስገንዘብ ይገባል። “ገቢዎች መጡ” ብሎ ንብረት ከሚያሸሽ ሰው ልጁ ምን ሊማር ይችላል፡፡ የሀገር ፍቅር የሚገለጸው በቅንነትና በሀቀኝነት ለሀገር ሁነኛ አስተዋጽኦ ማበርከት ሲቻል በመሆኑ በዚህ ልክ ትውልዱን መቅረጽና ማስተማር ከእያንዳንዱ ቤተሰብ መጀመር አለበት፡፡ መልካም ነገር የተቀበለ ትውልድ መልካም ነገር ያስቀጥላል፡፡ በዚህ ረገድ የመንግስት ድርሻም ከፍተኛ መሆን አለበት፡፡ የማህበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ስልጠና ከመስጠት ጀምሮ የተለያዩ ማስታወቂያዎችን በተደጋጋሚ መስራት ይኖርበታል፡፡ ለተወሰነ ጊዜ በሚዲያ ብቻ አስነግሮ ማቆም ሳይሆን በየተቋማቱ፣ ሰው በሚሰበሰብባቸው በተለያዩ አካባቢዎች፣ በየታክሲዎች ለማስተዋወቅ ትኩረት መስጠት ይጠበቅበታል፡፡

በለይላ መሀመድ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review