ኪነ ጥበባዊ መሰናዶዎች

You are currently viewing ኪነ ጥበባዊ መሰናዶዎች

በአብርሃም ገብሬ

በመዲናችን የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ስራዎች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል፡፡ ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም በመዲናችን የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች የተሰናዱ ሲሆን፣ ከእነዚህ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች መካከል የሥዕል አውደ ርዕይ፣ የመጽሐፍት ምረቃ፣ የቴአትር መርሃ ግብር እና ሌሎች መሰናዶዎች ይገኙበታል፡፡ ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል መርሃ ግብሮቹን እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡

መጻሕፍት

በጋዜጠኛ መኮንን ወ/አረጋይ የተዘጋጀውና በርካታ ጉዳዮች የተካተቱበት “እነሆ ስንክሳር” የተሰኘ መጽሐፍ ለንባብ ሊበቃ ነው። በሸገር 102.1 ኤፍ ኤም ሬድዮ ለዓመታት ሲተላለፈ የቆየው “ስንክሳር” የሬድዮ ፕሮግራም አሁን በመጽሐፍ መልክ እንደተዘጋጀም ኢቨንት አዲስ ሚዲያ ዘግቧል፡፡

መጽሐፉ በጃፋር እና በዕውቀት በር መጻሕፍት መደብሮች በኩል አንባብያን እንደሚያገኙትም ተጠቁሟል፡፡ ከዚህ ቀደም በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ሬድዮ ላይ በሚያቀርባቸው የስንክሳር፣ የማሟሻ፣ የሐኪምዎ መልዕክት፣ የአርብ ምሽት ቆየት ያሉ ሙዚቃዎች እና በኤን ቢ ሲ ቴሌቪዥን በልዩ ልዩ ዝግጅቶች የምናውቀው ጋዜጠኛ መኮንን ወ/አረጋይ “እነሆ ማሟሻ” የተሰኘ የመጀመሪያ ቅጽ አንድ እና ተከታዩን ቅጽ ሁለት መጻሕፍትን በተከታታይ ከዚህ ቀደም ለአንባቢያን ማድረሱ ይታወሳል።

ሥነ-ጥበብ

“ጉራማይሌ” የተሰኘ የሥዕል አውደ-ርዕይ በመታየት ላይ ነው፡፡ በሰዓሊ አበራ መሃሪ የተሳሉ ሥዕሎች የቀረቡበት ጉራማይሌ የሥዕል አውደ-ርዕይ ፈንድቃ የባሕል ማዕከል እና ሀያት ሬጀንሲ ሆቴል በመተባበር ባለፈው ግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ነው የተከፈተው፡፡ አውደ ርዕዩ እስከ ፊታችን ሰኞ ግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ለተመልካች ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡ የሥዕል ዓውደ-ርዕዩ እየታየ ያለው ሀያት ሬጀንሲ ሆቴል ውስጥ በሚገኘው በፈንድቃ የባሕል ማዕከል መሆኑ ታውቋል፡፡

በሌላ መረጃ የጣይቱ የባህልና ትምህርት ማዕከል የመጀመሪያ የስዕል ኤግዚቢሽን ለህዝብ ክፍት ሆኗል። “ጣይቱ” የተሰኘ ከ24 በላይ የታዋቂ አንጋፋና ወጣት ሰዓሊያን የተሳተፉበት የሥነ ጥበብ ትርኢት በታሪካዊው የአዲስ አበባ የመጀመሪያ ማዘጋጃ ቤት በነበረውና በአሁኑ የጣይቱ የባህልና ትምህርት ማዕከል ውስጥ ባሳለፍነው ሳምንት ሰኞ ጀምሮ ለህዝብ ክፍት ሆኗል፡፡ በዚህ ዐውደ ርዕይ ላይ ከሥዕል በተጨማሪ ልዩና ደረጃቸውን የጠበቁ ኪነ ቅርጾችም መቅረባቸው ታውቋል። ይህ  የሥዕል አውደ ርዕይ ለ15 ቀናት (እስከ ግንቦት 30 ቀን) ክፍት ሆኖ እንደሚቆይም ታውቋል። ይህ አጋጣሚ እንደ አዲስ የተጠገነውን ታሪካዊ ቅርስ ቤቱን ለመጎብኘትም ታላቅ እድል ጭምር በመሆኑ የጥበብ አፍቃሪያን የሥዕል አውደ-ርዕዩን እንዲጎበኙ ተጋብዘዋል፡፡ የሥዕል አውደ ርዕዩ እየታየ ያለው፣ አራዳ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ጎን ነው፡፡

በሌላ መረጃ “የተሸመኑ ትውስታዎች” የሥዕል አውደ ርዕይ በመታየት ላይ ነው፡፡ በወጣቱ ሠዓሊ ብርሃኑ ማናዬ የተዘጋጁ ሥዕሎች የቀረቡበት “የተሸመኑ ትውስታዎች” የሥዕል አውደ ርዕይ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ግንቦት 2 ቀን 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ ፖስታ ዋና መስሪያ ቤት ውስጥ በሚገኘው “The Space Ethiopia” የሥዕል ማሳያ ውስጥ ለእይታ በቅቷል። በዳግም አበበ አጋፋሪነት የተዘጋጀው ይህ አውደ ርዕይ የተለያዩ የሥዕል አቀራረቦችን እንዲሁም በተለያዩ የአሳሳል ዘይቤ የተሰሩ የሥዕል አይነቶችን ያካተተ እንደሆነ ተገልጿል። አውደ ርዕዩ እስከ ሰኔ 18 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በእይታ ላይ ይቆያል ተብሏል።

ሙዚቃ

“አስኒ” የተሰኘው ሙዚቃዊ ፊልም ቀጣይ ሳምንት ለእይታ ይበቃል፡፡ በድምጻዊት አስናቀች ወርቁ ሕይወትና ስራዎች ላይ ትኩረቱን ያደረገው “አስኒ” የተሰኘ ፊልም የፊታችን ሐሙስ ግንቦት 28 ቀን 2017 ዓ.ም ከምሽቱ 11:30 ሰዓት ጀምሮ ሳህሊተ ምህረት ቤተ ክርስቲያን አካባቢ በሚገኘው በቬኒው ዌርሃውስ ውስጥ ለእይታ ይበቃል።

ፊልሙ ከታየ በኃላም “የአስናቀች ወርቁ  የሕይወት ታሪክ፤ ድፍረት፣ ጥልቅ ስሜት እና ውበት በኢትዮጵያ” የተሰኘ ርዕስ የተሰጠው ውይይት ከፊልሙ አዘጋጅ ራሔል ሳሙኤል ጋር ውይይት ይካሄዳል ተብሏል።

የቴአትር መርሃ ግብር

በመዲናችን አዲስ አበባ ቅዳሜ እና እሁድ ከሚታዩ ቴአትሮች ውስጥ  የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡ በብሔራዊ ቴአትር ቤት ባሎች እና ሚስቶች የተሰኘው ቴአትር ቅዳሜ 8:00  ሰዓት፤ 11፡30 ሰዓት ደግሞ ባቡሩ የተሰኘው ቴአትር የሚታይ ሲሆን፤ እሁድ ዕለት በቴአትር ቤቱ በ 8፡00 ሰዓት 12ቱ እንግዶች ቴአትር ለእይታ የሚቀርብ ይሆናል፤  እምዬ ብረቷ ቴአትር 11፡30 ሰዓት ላይ ይታያል፡፡ እንዲሁም በቀጣይ ቀናት በብሔራዊ ቴአትር የሚታዩት ማክሰኞ በ11፡30 ሰዓት ሦስቱ አይጦች፣ ረዕቡ በ11፡30 ሰዓት የቅርብ ሩቅ ቴአትር፣ ሐሙስ 11:30 ሰዓት ሸምጋይ ቴአትር፣ አርብ በ11፡30 ሰዓት የሚታይ ሲሆን፣ በዓለም ሲኒማ “ጥቁር እንግዳ” ተውኔት ሐሙስ በ12፡00 ሰዓት ለጥበብ አፍቃሪያን ለዕይታ ይቀርባሉ፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review