ከጋዜጣዋ ቀደምት ይዘቶች ለቅምሻ

You are currently viewing ከጋዜጣዋ ቀደምት ይዘቶች ለቅምሻ

በመገናኛ ብዙሃን ታሪክ ውስጥ የህትመት ውጤቶች ታሪክ የረዘመ ዕድሜ አላቸው፡፡ ከእድሜም ባሻገር የዘመናዊ ዓለም ውልደት ከህትመት ውጤቶች ጋር ጥብቅ ትስስር አለው፡፡ በፈረንጆቹ 1468 በጀርመናዊው ሳይንቲስት ዮሐንስ ጉተንበርግ የተፈጠረው የህትመት ማባዣ ወይም ማሳተሚያ ማሽን የዘመናዊ ዓለም ውልደትን ያበሰረ ክስተት ነው፡፡ የዚህ ማሽን መፈጠር የመረጃ ፍሰቱን በፍጥነት በመለወጥ እንደ ህዳሴ ዘመን (ሬነሰንስ) ያሉ የዘመናዊነት አዋላጅ የዘመን እንቅስቃሴዎች እንዲፈጠሩ ማድረግ ችሏል፡፡ የጋዜጦች ህትመትና ውልደትም ከዚህ የዘመን እንቅስቃሴ ጋር የተሳሰረ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክም የጋዜጦች አስተዋጽኦና ሚና እጅግ ከፍተኛ መሆኑ የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ፡፡ በተለይ በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ጊዜ ከተጀመረው “አዕምሮ” ጋዜጣ በኋላ ወደ ህትመት የገባው “ብርሃንና ሰላም” ጋዜጣ፣ በሀገሪቱ መልከ-ብዙ የለውጥ ጉዞዎች ላይ ትልቅ ሚና እንደነበረው ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ የጋዜጦች ሚና በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳላቸው መረዳት ይቻላል። ከእነዚህ ጋዜጣዎች መካከል የመዲናዋን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በመዘገብ ከትናንት እስከ ዛሬ የተሻገረችው አዲስ ልሳን ጋዜጣ ትጠቀሳለች፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍም የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ሰላሳ ሁለተኛ ዓመቷን ተከትሎ፣ የጋዜጣዋ ጉዞ ከየት ተነስቶ እዚህ እንደደረሰና ጋዜጣዋ በቀደሙት ህትመቶቿ ምን ምን ጉዳዮችን አስነብባ ነበር የሚለው ጉዳይ ላይ አጭር ዳሰሳ እንደሚከተለው አድርገናል፡፡

የአዲስ ልሳን ጉዞ

አዲስ ልሳን ጋዜጣ የተመሰረተችው ግንቦት 20 ቀን 1985 ዓ.ም ነበር። የቀድሞው የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ የአሁኑ የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ምስረታ ግንቦት  1985 ዓ.ም ከተቋቋመው ከዚሁ አዲስ ልሳን ጋዜጣ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ በሂደትም ከጋዜጣው በተጨማሪ የኤፍ.ኤም 96.3 ሬዲዮን እና አዲስ ቴሌቪዥንን በመጨመር የሚዲያ ስራውን አስፋፍቷል፡፡

አዲስ ልሳን ጋዜጣ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አንባቢዎቿ የደረሰችው ግንቦት 20 ቀን 1985 ዓ.ም ነበር፡፡ በወቅቱ በነበረው የአዲስ አበባ ማስታወቂያና ባህል ቢሮ ስር ሆና ስራዋን የጀመረችው ጋዜጣዋ፣ በሒደት የሬዲዮና ቴሌቪዥን፣ እንዲሁም የማህበራዊ ሚዲያው ዘርፍን በማቀፍ አሁን ደረጃ ላይ ለደረሰው አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ መሠረት መሆን ችላለች፡፡

ከምስረታዋ ወቅት ጀምሮ እስከ 1987 ዓ.ም ድረስ በ8 ገጾች በየ15 ቀኑ ስትታተም ቆይታለች፡፡ ጋዜጣዋ ላይ በተደረገ አንድ ጥናት ላይ እንደሰፈረው፣ ጋዜጣዋ ከተመሰረተች በኋላ “የአምድ ዐቢይ ርዕሰ ጉዳዮች ያልነበሯት ሲሆን፣ ይህም ወጥነት ያለው የከተማዋን ጉዳዮች ለመዳሰስና መደበኛውን የጋዜጠኝነት አሰራር ተከትሎ ለመስራት ተቸግራ እንደነበር ተመላክቷል፡፡ ሆኖም ከየካቲት 1987 ዓ.ም ጀምሮ የገጽ ብዛቷን ወደ 16 በማሳደግና ዐቢይ ርዕሰ ጉዳዮችን በመያዝ ወደ አንባብያን መድረስ ጀምራለች፡፡ 

በሒደትም በ1988 ዓ.ም በሳምንት ሁለት ጊዜ ማለትም ረቡዕ እና ቅዳሜ በመታተም አንድ እርምጃ ወደ አንባቢዎቿ ተጠጋች፡፡ በእነዚህ እትሞች ደግሞ እንደ ዝክረ ቅዳሜ፣ አዲስ እንግዳ እና ከህዝብ አንደበት ያሉ የመዝናኛ እና የነዋሪዎችን ተሳትፎ የሚያሳድጉ ገጾችን አካተተች፡፡ አዲስ ልሳን እንዲህ እንዲህ እያለች በከለር የሚታተሙ ገጾችንም እያካተተች ተጓዘች፡፡ በ2008 ዓ.ም ደግሞ ጋዜጣዋን በመሰረቱ ሊያሻሽል የሚችል የይዘትና ቅርጽ ጥናት ተጠንቶ የተወሰኑ መሻሻሎችን አድርጋለች፡፡ ጋዜጣዋም አዳዲስ አምዶችን በማከል፣ በሳምንት ሁለት ጊዜ ይታተም የነበረውንም ወደ ሦስት በማሳደግ ይበልጥ ወቅታዊነቷንና ተደራሽነቷን ለማስፋት ጥረት ተደርጓል፡፡

ሆኖም ጋዜጣዋ በህትመት ጥራትና በይዘት ደረጃ ውስንነቶች በመታየታቸው፣ በ2016 ዓ.ም ይህንን ውስንነቶች ለመቅረፍ የሚያስችል ሌላ ጥናት ተደርጓል፡፡ በዚህ ጥናት ላይ አዳዲስ የሙያተኞች ሃሳብና የሌሎች ጋዜጦች ተሞክሮን በማከል በያዝነው በ2017 ዓ.ም ጋዜጣዋ መሰረታዊ ለውጥ አድርጋ ለአንባቢያን መድረስ ጀምራለች፡፡ ከጥቂት ወራት ወዲህ ጋዜጣዋ በህትመት ጥራትዋም ሆነ በይዘት ደረጃዋ ተሻሽላ በሳምንት ቅዳሜ አሁን በምናያት መልክ ለአንባቢያን ትደርሳለች፡፡

የጋዜጣዋ አበርክቶ

የዛሬ ዜናዎች የነገ ታሪኮች ናቸው። የዘመኑን ሁኔታና መልክ እንድንረዳ የሚያስችሉን መስታወቶችም ጭምር፡፡ በታሪክ ሂደት ውስጥ ከየት ተነስተን እዚህ ደረስን የሚለው ጉዳይ ለመረዳት ያለፉት ጋዜጦች ሚና እጅግ የላቀ ነው፡፡ ‘አዲስ ልሳን’ ጋዜጣም ከተመሰረተችበት ጊዜ አንስቶ በአዲስ አበባ ከተማ፣ በሀገሪቱና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች፤ እንዲሁም በማህበራዊና በኪነ ጥበባዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ይዘቶችን ለአንባቢያን እያደረሰች እዚህ ደርሳለች፡፡

የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍልም ባደረገው አጭር ቅኝት፣ ትልልቅ የሚባሉ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ኩነቶችን ሽፋን ሰጥታለች፡፡ እንዲሁም የሀገር ባለውለታዎችን በኪነ ጥበብ አምዷ ላይ ዘክራለች፡፡ አልፎ አልፎ በዜና እና በሌሎች አምዶቿ ላይ በዚህ ዘመን ላይ ላለ ሰው ፈገግታን የሚያጭሩ ርዕሰ-ጉዳዮችን በጋዜጣዋ ተስተናግደዋል፡፡

ለአብነትም በነሐሴ 10 ቀን 1985 ዓ.ም በታተመችው አዲስ ልሳን ጋዜጣ የፊት ገጽ ላይ “ባንኩን ያተራመሱ አይጦች” በሚል ርዕስ የወጣ ጽሑፍ አስገራሚም አስቂኝም ነው፤ “ከፍተኛ ጥንቃቄና ጥበቃ የሚደረግለት ብሔራዊ ባንክ ኮምፒዩተር ኬብል በመበጣጠሱ በደረሰው የሃይል መቋረጥ ዋናውን ባንክ ጨምሮ ስድስት ቅርንጫፎች ለሦስት ቀናት አስተጓጉሎባቸው መሰንበቱን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አስታውቋል፡፡ በዚህ ጥፋት ሳቢያ የደረሰ ኪሳራ እንደሌለ አንድ የባንኩ ኃላፊ ቢናገሩም ይህን መሰሉን ስውር አደጋ ያደረሰውን ወንጀለኛ አድኖ ለማግኘት በተደረገው ርብርብና ክትትል አይጦች መሆናቸው ተደርሶበታል” ይላል የጋዜጣዋ ዘገባ፡፡ ዘገባው ምንም እንኳን ፈገግታ የሚያጭር ቢሆንም፣ የዘመኑ የእድገት እና የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ደረጃን በሚገባ ለመረዳት ያግዛል፡፡

ሌላው በጋዜጣዋ “ዓውደ-ባህል” አምድ ላይ ይስተናገዱ የነበሩ የሀገራችን ከያኒያን ህይወትና ስራዎች ዛሬ ላይ ሆነን ብናነባቸው እንኳን ትኩረት የሚስቡ ርዕሰ-ጉዳዮች ናቸው፡፡ በዚህ ዓምድ ላይ ይወጡ የነበሩ ተደጋጋሚ ጽሑፎች ይጻፉ የነበሩት በታምራት ሃይሉ ነበር፡፡ ታምራት ሃይሉ ኋላ ላይ በግሉ ፕሬስ ዘርፍ ተሰማርቶ “ቁም ነገር” የተሰኘ መጽሔት በመመስረትና የመጽሔቷ ማኔጂግ ኤዲተር እንደነበር የሚታወስ ነው። በዚህ ዓውደ ባህል ላይ ከተስተናገዱ ጽሑፎች መካከል፣ መስከረም 14 ቀን 1992 ዓ.ም “የሀዲስ አለማየሁ አስተዋጽኦ በአማርኛ ሥነ ጽሑፍ”፣ “ወጋየሁ የሞተ ዕለት ብሞት ደስ ይለኝ ነበር” በሚል ርዕስ ሐምሌ 22 ቀን 1992 የጋዜጣዋ ዕትም እና ጥቅምት 25 ቀን 1993 ዓ.ም ዕትሟ ላይ የባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን ሥራዎችና ህይወት ያስቃኘችበት ጽሑፍ ጥሩ ማሳያዎች ናቸው፡፡

ከዚያም በኋላ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት፣ ብሔራዊ ምርጫዎችን፣ የ2010 ዓመተ ምህረቱን የፖለቲካ ለውጥ፣ የኮሪደር ፕሮጀክቱን እና ሌሎችንም መዝናኛ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ከተማና ሀገር አቀፍ ጉዳዮችን በዜና እና በትንታኔ መልክ ለአንባቢዎቿ እያደረሰች የበኩሏን አስተዋጽኦ ስትወጣ ቆይታለች፤ በመወጣት ላይም ትገኛለች፡፡

በአጠቃላይ ጋዜጣዋ ከትናንት እስከ ዛሬ በተለያዩ የታሪክ እጥፋቶች ውስጥ በማለፍ አሁን ያለንበት ጊዜ ላይ ደርሳለች። ጋዜጣዋ እዚህ ለመድረስ ብዙ ውጣ ውረዶችን ማለፏ ከቀደሙት እትሞቿ መረዳት ይቻላል፡፡ በእነዚህ ህትመቶቿ ባለፉት ሠላሳ አንድ ዓመታት ውስጥ በሀገሪቱ የተከሰቱ ኩነቶችን እና የአዲስ አበባ ጉዳዮችን ሽፋን በመስጠት ዛሬ ላይ ደርሳለች፡፡

ጋዜጣዋ አሁን

አሁን ወቅቱን በሚመጥን እና ተወዳዳሪ ሆኖ መቅረብ በሚያስችል መልኩ ማሻሻያዎችን አድርጋለች፡፡ በጥናት ላይ በተመሰረተ፣ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ጋዜጣዎች ያሉበትን ቁመና ከግምት ባስገባ መልኩ ጥናት በማድረግ የይዘት እና የሌይአውት ማሻሻያ አድርጋ ዘወትር ቅዳሜ ወደ አንባቢያን ተደራሽ በመሆን ላይ ትገኛለች፡፡

በአብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review