የካዛንቺሱ የልም አሽዋ መጫወቻ ምን ይዟል?

You are currently viewing የካዛንቺሱ የልም አሽዋ መጫወቻ ምን ይዟል?

በቅርቡ በካዛንቺስ ተገንብቶ ለአገልግሎት የበቃው የልም አሸዋ መጫወቻ ስፍራ (sand box) አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን በልጅነት ጊዜያቸው ያሳለፉትን ገፅታ የሚመልስ ሆኗል፡፡

በቀዳማዊ ልጅነት ፕሮጀክት አማካኝነት የተገነባው የልም አሸዋ መጫወቻ ስፍራ (sand box) ምን ምን እንደያዘ፣ ለልጆች መዝናኛነት በምን መልኩ እንደሚያገለግል እንዲሁም ወደ ሥፍራው የሄዱ ልጆች በነበራቸው ቆይታ የተፈጠረባቸው ስሜት ምን እንደሚመስል የዝግጅት ክፍላችን ያደረገውን ቅኝት ለእናንተ ለልጆች በሚሆን መልኩ እናቀርበዋለን፡፡

ፅዮን ሀይሉ ትባላለች፡፡ እድሜዋም አምስት ዓመት ሲሆን የኬጂ 2 ተማሪ ነች። ፅዮንን ያገኘናት በካዛንችስ በተሠራው የልም አሸዋ መጫወቻ ስፍራ ከወላጅ እናቷ ጋር በመሆን ስትዝናና ነው። እሷም ስለ አዲሱ የመጫወቻ ስፍራ፤ “እዚህ መጥቼ በመጫወቴ የተለየ ደስታ ሰጥቶኛል፡፡ የአሸዋው ልስላሴ ደስ ይላል። በአሸዋው ዳቦ፣ ዶናት  እና ሌሎች ክብ  ቅርጾችን ሰርቻለሁ፡፡ እናቴም የተለያዩ ቅርጽ ማውጫ ነገሮችን ገዝታልኛለች። ይህንን አይነት ጨዋታ ከዚህ ቀደም ተጫውቼ አላውቅም፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የተጫወትኩት፡፡ ስጫወት ምንም አይደክመኝም፤ አይሰለቸኝም ደስ ነው የሚለኝ” ብላለች፡፡

የህጻን ፅዮን ወላጅ እናት ወይዘሮ ቤተልሄም ድንቅነህ ከ6 ኪሎ እንደመጡና የልም አሸዋ መጫወቻ ስፍራ ለልጃቸው ልዩ ደስታ ስለፈጠረላት  ተደስተዋል። “ልጄ አዲሱን የመጫወቻ ሥፍራ በቴሌቪዥን ካየችው ጀምሮ  እንድወስዳት ደጋግማ ትጠይቀኝ ነበር፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ከወሰድኳት በኋላ በተደጋጋሚ የመምጣት ፍላጎቷ ጨምሯል፡፡ መጫዎቻው ጋር ከደረሰች ረጅም ሰዓት ትጫወታለች፡፡ ከዚህ ቀደም የተለያዩ የመጫወቻ ስፍራዎች እወስዳት ነበር። እንደዚህ ግን የወደደችው የመጫወቻ ስፍራ የለም፡፡ ሸርታቴ ስትጫወትም እግሯ የሚያርፈው አሸዋው ላይ ስለሆነ ለጉዳት አይዳርጋትም፡፡ ከቦታው መሄድ አትፈልግም፡፡ በግድ መሸ ብዬ ነው 12 ሰዓት አካባቢ ወደ ቤታችን የምንሄደው።” ሲሉ መጫወቻ ስፍራው ለልጃቸው የፈጠረውን ስሜት ነግረውናል፡፡

ሌላኛዋ በካዛንቺሱ የልም አሸዋ መጫወቻ ስፍራ ስትጫወት ያገኘናት  የ3ኛ ክፍል ተማሪዋ ህጻን ራኬብ ወንድሙ ነች፡፡ “የመጫወቻ ስፍራው ደስ ይላል፡፡ አሸዋውን በእጄም በእግሬም ብነካካው እንደ አፈር አያቆሽሸኝም፡፡ ከላይ ተንሸራትቼ የማርፈውም አሸዋው ላይ ስለሆነ እግሬን ደስ ይለዋል፡፡ እሚጎረብጥ ነገር የለውም፡፡ የመኖሪያ ቤቴ ካዛንችስ ኮንዶምንየም በመሆኑ በየቀኑ እየመጣሁ ለመጫወት እድል ሰጥቶኛል፡፡ ሰፈሬ ላይ እንዲህ አይነት ደስ የሚል መጫወቻ በመሰራቱ ደስ ብሎኛል” ብላለች፡፡

የ4ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ህጻን ሞሴ ዮርዳኖስም በተመሳሳይ ስሜቱን እንዲህ ሲል ገልጿል፤ “የመኖሪያ ቤቴ በዛው ካዛንችስ አካባቢ ከመሆኑ የተነሳ ከሰኞ እስከ አርብ ያሉትን ቀናት ሁሉ ከትምህርት ቤት መልስ ቀን በቀን እየመጣሁ እጫወታለሁ፡፡ በአካባቢው የተለያዩ መጫወቻዎች የተሰሩና የሚያዝናኑ ቢሆንም ይህ በአሸዋ የተለያዩ ቅርጾችን እየሰሩ መጫወት ግን የተለየ ደስታ ይሰጠኛል፡፡ በእግሬ ስረግጠውም ደስ ይለኛል፡፡  አሸዋውን በእጄ ስነካካውም የተለየ ስሜት ይሰጠኛል፡፡ በውስጤ የማስበውን ሀሳብ እና የምፈልገውን ነገር ለመስራት ይመቻል፡፡ እስካሁን ባለው ኳስ፣ ኳስ ሜዳ እና የመሳሰሉ ቅርጾችን በመስራት ከጓደኞቼ ጋር እወዳደራለሁ፡፡”  

ከመሳለሚያ እህል በረንዳ አካባቢ ልጃቸውን ለማዝናናት የመጡት አቶ መሀመድ አማን፤ ልጃቸው የመጫወቻ ስፍራውን በቴሌቪዥን አይቶ ደጋግሞ “ውሰደኝ” ስላላቸው ነው ይዘውት የመጡት፡፡ እሳቸው ልጃቸውን እዚህ ይዘው በመምጣታቸው በጣም ተደስተዋል፡፡ ልጃቸውም ጥሩ የጨዋታ ጊዜ አሳልፏል፡፡ አቶ መሃመድ፤ “ይህ መጫወቻ ስፍራ በሁሉም ደረጃ ለሚገኝ ቤተሰብ ልጆችን ለማዝናናት የሚሆን ነው፡፡ እንዲህ አይነት ተመሳሳይ መጫወቻ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ላይ  ቢሰራ ጥሩ ነው፤ በክፍለ ከተማው አንድም የለም” ሲሉም ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡ 

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት የቀዳማዊ ልጅነት የመጫወቻ ቦታ  ላንድ ስኬፕ አርክቴክት ማሪያማዊት መስፍን፤ የልም አሸዋ የመጫወቻ ስፍራ (sand box) ለህጻናት ስለሚሰጠው ፋይዳ ለዝግጅት ክፍሉ እንደሚከተለው አብራርተዋል።  ከ6 ወር እስከ 7 ዓመት ድረስ ያሉ ህጻናትን ማዕከል ያደረገው የቀዳማይ ልጅነት የመጫወቻ ቦታ ከሌላው የተለየ ነው፡፡ ለህጻናት አእምሮና ለአካል ደህንነት እንዲሁም ለማህበራዊ ግንኙነታቸው ጥቅም የሚሰጥ ነው፡፡ ልጆች አሸዋው ላይ ተቀምጠው በሚጫወቱበት ወቅት የአሸዋውን ቀለም እና ስሪት በማየት እንዲመራመሩ ያደርጋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በአሸዋው ውስጣቸው የሚፈልጉትን የተለያዩ ነገሮች በመስራት አዲስ ነገር ለመፍጠር የሚያስችላቸውን ክህሎት ያዳብርላቸዋል፡፡ የህጻናትን ማህበራዊ መስተጋብር በማጎልበት ረገድም ጉልህ ፋይዳ እንዳለው አርክቴክት ማሪያማዊት ተናግረዋል፡፡

ልጆችዬ አሁን አሁን ትኩረታችሁን እየሳበው ያለው የስልክና ኮምፒውተር ጌሞች አይናችሁን ጨምሮ  እንደ የወገብ በሽታ የመሳሰሉ አካላዊ ጉዳቶችን የሚያስከትሉባችሁ በመሆናቸው እንዲህ አይነት ጨዋታዎችን በማዘውተር አካላዊ ደህንነታችሁን መጠበቅና ማህበራዊ መስተጋብራችሁን ማዳበር አለባችሁ ሲል የዝጅግት ክፍሉ መልዕክቱን በማስተላለፍ መልካም የጨዋታ ጊዜ እንዲሆንላችሁ ተመኝቷል፡፡    

በለይላ መሀመድ

 

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review