ፓሪሰን ዠርማ ኢንተር ሚላንን 5ለ0 አሸንፎ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ሲያነሳ ደስታው ልዩ ነበር።
በሙኒክ አልያንዝ አሬና የተገኘው ድል ፓሪስን አናውጧል። በሚንቀለቀል ስሜታዊ ድጋፋቸው የሚታወቁት የፓሪሰን ዠርማ ደጋፊዎች የትላንት ምሽቱ ደስታ አገላለፃቸው ጣጣ ይዞባቸው መጥቷል።
ቢቢሲ ባጠናቀረው ዘገባ ገና ጨዋታው ሳያልቅ የጀመሩት ከልክ ያለፈው ድጋፋቸው ከፖሊስ ጋር ግጭት ውስጥ ከቷቸዋል።
ከፓሪስም ውጪ በነበረው በዚህ ስርዓት አልበኝነት ሁለት ወጣቶች ሕይወታቸው እንዲቀጠፍ ምክንያት ሆኗል።
በደቡብ ምዕራብ ዳክስ ከተማ ላይ የ17 ዓመት ታዳጊ በስለት ተወግቶ እንደሞተ የሀገሪቱ አቃቤ ህግ ገልጿል።
በፓሪስ ስኩተር እየነዳ ደስታውን ሲገልፅ የነበረ የ23 ዓመት ወጣትም ከመኪና ጋር ተጋጭቶ ሕይወቱን አጥቷል።
በአጠቃላይ በሁከቱ 192 ሰዎች ሲጎዱ 559 ለእስር ተዳርገዋል። ከ264 በላይ መኪኖች በቃጠሎ ጥቅም አልባ ሆነዋል።
22 ፖሊሶች እና ሰባት የእሳት አደጋ መከላከል ሰራተኞች የሁከቱ ገፈት ቀማሽ ሆነው ጉዳት እንደደረሰባቸው የቢቢሲ ዘገባ ያሳያል።
የፈረንሳይ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ብሩኖ ሬቴይሊው ድርጊቱ እውነተኛ የፓሪሰን ዠርመ ደጋፊዎችን አይወክልም ብለዋል።
አጋጣሚውን የተጠቀሙ ጥፋተኞች ለዚህ ሁከት ተጠያቂናቸው ሲሉ ተናግረዋል።
ትናንት ምሽት በተለይ እግርኳስ ለሚወዱ ፓሪሳዊያን ልዩ ምሽት ቢሆንም ሁከቱ በመጠኑ ደስታቸውን አደብዝዞባቸዋል።
በተቻለ መጠን ግን ድሉን ለማጣጣም ጥረዋል። የፈረንሳይ ትልቁ ቅርስ ኤፍልታወር በፓሪሰን ዠርመ አርማ አሸብርቆ ነበር።
የፒ ኤስ ጂ ተቀናቃኝ ማርሴይ ደጋፊ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ኤማንኡል ማክሮን በX ገፃቸው “አስደናቂ ድል ለፒ ኤስ ጂ ሁላችንም በድላቹህ ኮርተናል። ፓሪስ የአውሮፓ ቁንጮ ሆናለች” ሲሉ የደስታ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ፓሪሰን ዠርማ የቡድን አባላቱ ወደ ፓሪስ ሲመጡ ድሉን በጎዳና ላይ ያከብራል። መሰል ሁከቶች እንዳይነሱ ከወዲሁ ስጋት አለ።
በሸዋንግዛው ግርማ