የኢትዮጵያ ብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ባለቤት መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ገልፀዋል።
ብዝሃ ዘርፍ፣ ብዝሃ ተዋናይ፣ ብዝሃ ተጠቃሚ ካልሆነ በቀር በአንድ ዘርፍ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያን ስብራቶች አይጠግንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት 5 ዘርፎች ላይ በዋነኛነት ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በአፍሪካ ርካሽ የሰው ሃይል፣ ርካሽ ጥሬ እቃ አለ ከሚል እሳቤ አንፃር መንግስት እንደ አገልግሎት ዘርፉ ሁሉ ለኢንዲስትሪ ለምን ሰፊ ትኩረት አልሰጠም በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ምርት አምርቶ በአለም ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን የሎጂስቲክስ ውስንነት ከችግሮቹ ዋነኛው መሆኑን አንስተዋል።
የሰው ሰራሽ አስተውሎት እየተስፋፋ ከመምጣቱና በሰዎች ይሰሩ የነበሩ ስራዎች በሮቦቶች እየተሰሩ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሰው ሃይል ዘላቂ መወዳደሪያ መሆን እንደማይችል አመላክተዋል።
ለፕላስቲክ፣ ለብረትም ሆነ ለመስታወት የሚሆን ጥሬ እቃ ግብአት ቢኖርም አለም ላይ ካለው የመልሶ መጠቀም ስርአት አንፃር ቀድሞ የወጣውን ሃብት እንዴት ለመልሶ መጠቀም ማዋል እንደሚቻል መጠየቅ አስፈላጊ መሆኑንም አመላክተዋል።
በኢንዲስትሪው ዘርፍ ከፍተኛ ለውጥ መኖሩን ያመላከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከለውጡ በፊት 48 በመቶ አካባቢ ምርት ብቻ ያመርቱ የነበሩትን ችግሮቻቸውን በመፍታት 65 በመቶ ምርት ማምረት መቻሉን ጠቁመዋል። የኢንዱስትሪያል ፓርኮቹንም ቁጥር ከ3 ወደ 13 ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።
በኢንዱስትሪው እስካሁን ድረስ ፈሰስ ሲደረግ ነበር ፣ አሁን ምላሽ የሚያሳይበት ጊዜ ደርሷል ያሉ ሲሆን በዚህ አመት 13 በመቶ እድገት ያሳያል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።
መንግስት ዘመን ገበያ የተሰኘ የዲጂታል ገበያ ስራ ማስጀመሪን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዲጂታል ገበያው ሻጩን ከሸማቹ በማገናኘት መሃል ባሉ ደላሎች ምክንያት የነበረውን እንግልት እና የዋጋ ውድነት አንደሚቀርፍ ተናግረዋል። ገበያው ስራ በጀመረበት 20 ቀናት ውስጥም 4 ሚሊየን ብር ሽያጭ ማካሄዱንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።