ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል መንግስት እያከናወነ ያለውን ተግባር አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸውም፣ ሌብነት አንዱ የጥፋት መንገድ እና ስብራት ነው ያሉ ሲሆን፣ ካልተገራ በስተቀር በመትጋት ላይ ላለች ሀገር እንቅፋት ነው በማለት አስገንዝበዋል።
ሰዎች ሰርቀው ህንፃ ቢገነቡ እንደ ስርቆት ሳይሆን ልቀው እንደተገኙ የሚያስብ ማህበረሰብ ብዙ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ሰራቂው ብቻ ሳይሆን የሚሰረቀውም የሚተባበርበት ልማድ እንደባህል መያዙ፣ ችግሩ እንደ ግለሰብ ብቻ ሳይሆን እንደ ማህበረሰብ ሥር የሰደደ ስብራት መሆኑን አመላክተዋል።
የዚህ አይነቱ ችግር በንግግር እና በፖሊሲ ብቻ ሊቀረፍ እንደማይችልም ነው የተናገሩት።
መሰል ችግሮች ውስጥ የገቡ ሰዎችን በጥናትም ሆነ በፀረ ሙስና በኩል ብዙ አሥረናል፣ አባረናል እንዲሁም ከቦታቸው ቀይረናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መሠረታዊ የባህል ለውጥ ባለመኖሩ ግን ለውጥ አለመምጣቱን አንስተዋል።
ችግሩን ከመሠረቱ ለመቅረፍም መንግስት የተለያዩ ስልቶችን መከተሉን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የመጀመሪያው ተቋማዊ ሌብነትን ማስቆም ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ላይ መንግስታዊ ሌብነት አለመኖሩንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።
በመንግስት ደረጃ የተገኘውን በየትኛውም መጠን ያለ ገንዘብ የምናውለው ለልማት ብቻ ነው ሲሉም አክለዋል።
በተለይም በቡድን የተደራጁ ሀይሎች በተቀናጀ መልኩ ዘረፋ ሲፈፅሙ የሀገር ዕድገት እንደሚጎዳ አስገንዝበዋል።
አሁን ላይ ግን በዚህ ደረጃ የሚፈፀም ሙስና መቶ በመቶ አለመኖሩን ገልጸዋል።
ይህ ማለት ግን በግለሰብ ደረጃ የሚሰርቅ ሌባ ባለሥልጣን የለም ማለት አለመሆኑን ጠቅሰው፣ በተለያዩ ጊዜያትም ችግሩን መግታት የሚያስችል ራዕይ የመጋራት እና የግንዛቤ ሥልጠናዎች ለአመራሩ መሰጠቱን አብራርተዋል።
በከፍተኛ አመራር ደረጃ አብዛኛው መሰል ችግር ውስጥ የለበትም ሲሉም አክለዋል።
ሁለተኛው የትኩረት ምዕራፍ ደግሞ፣ ህዝብንም ለምሬት የሚዳርገው በአገልግሎት አሰጣጥ አካባቢ የሚስተዋለውና ብልሹ አሰራርን የመከላከል ሥራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለአብነትም በከተሞች አካባቢ ከመሬት ጋር ተያይዞ ሰፊ የብልሹ አሰራር ችግር እንደነበር አውስተው፣ አሁን ላይ የጂኦስፓሻል ሥርዓት መዘርጋቱን ተናግረዋል።
በርካታ አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ በዘመነ መንገድ የሚሰጥበት የመሶብ አገልግሎት ደግሞ ሌላኛው መንግስት ብልሹ አሰራርን ለመከላከል የሄደበትን ርቀት አመላካች መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ ለህዝብ እፎይታን የሚሰጥ ተቋም በክልል ከተሞችም በቀጣይ ጥቂት ወራት ውስጥ እንደሚጀመር ጠቁመዋል።
ሙስናን በመከላከል ረገድ ከትናንሽ ሌብነቶች ጀምሮ ህብረተሰቡ ሌባን የማጋለጥ ባህል ሊያዳብር እንደሚገባም አሳስበዋል።
በማሬ ቃጦ