የቆጣሪ ገጠማው የተከናወነው ኢንሄሜትር በሚባል የቻይና ኩባንያ ሲሆን፤ እስከ አሁን አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ 10 ሺህ የነጠላ ፌዝ እና 120 ባለ ሶስት ፌዝ ስማርት ቅድመ ክፍያ ቆጣሪዎች ገጠማ ማከናወኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገልጿል፡፡
የቆጣሪዎቹ ገጠማ ተግባራዊ የተደረገው በመካኒሳ ባቱ 1፣2፣3 እና 4 ኮንዶሚኒየም፣ ሰሚት መከላከያ ፋውንዴሽን፣ ባልደራስ ፈረስ ቤት ኮንዶሚኒየም፣ ባልደራስ የካ ሳይት 1 እና 2 ኮንዶሚኒየም፣ አያት አክሲዮን ቤቶች፣ ሃና ፉሪ ኮንዶሚኒየም ቤቶች፣ ሲ.ኤ.ም.ሲ ልዩ ቤቶች፣ ገርጂ ኮንዶሚኒየም 40/60 ቤቶች እና ኮዬ ፈጬ ኮንዶሚኒየም ሳይቶች ላይ መሆኑን አገልግሎቱ ለኤ ኤም ኤን በላከው መረጃ አስታውቋል፡፡
ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈለገው በዋናነት ከቅድመ ክፍያ የአከፋፈል ስርዓት እና ከድህረ-ክፍያ ከንባብ ጋር ያለውን ችግር በመፍታት የደንበኞችን እርካታ ለመጨመር ብሎም ባሉበት ቦታ ሆነው ስልካቸውን ብቻ በመጠቀም ኢነርጂ መግዛት የሚያስችላቸውን ስርዓት ለመፍጠር መሆኑን ጠቁሟል፡፡
ለተቋሙም በተለያየ ምክንያት የማይሰበሰብ ገንዘብን ለማስቀረት እንዲሁም አሰራሩን ሙሉ በሙሉ ዲጂታል ለማድረግ ታስቦ እንደሆነም አመላክቷል፡፡
እነዚህ ቆጣሪዎች ለነባር እና አዲስ ደንበኞች በመቀየር ደንበኞች ስልካቸውን ብቻ በመጠቀም ካሉበት ቦታ ሆነው ቶከን በቴሌ ብር በመግዛት ኤሌክትሪክ መጠቀም እንዲችሉ ለማድረግ ነው ብሏል፡፡
ፕሮጀክቱ የመጀመሪያ አላማ አድርጎ የተነሳው አምስት መቶ ሺህ ስማርት የቅድመ ክፍያ ቆጣሪዎችን መግጠም ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 150 ሺህ የሚሆኑት ስማርት ነጠላ ፌዝ ቆጣሪዎች ሲሆኑ፤ 350 ሺህ ቆጣሪዎቹ ደግሞ ነጠላ ፌዝ የኦፍላይን ቆጣሪዎች ናቸው፡፡
በዚሁ መሰረት በቀጣይ 15 ሺህ ስማርት ነጠላ ፌዝ ተጨማሪ ቆጣሪዎች ገጠማ በአዲስ አበባ ውስጥ የሚተገበር ሲሆን፤ 125 ሺህ የሶስት ፌዝ ስማርት ቆጣሪዎች እና 350 ሺህ የነጠላ ፌዝ ኦፍላይን ቆጣሪዎች ገጠማ ደግሞ በመላ ሀገሪቱ የመተግበር ስራ ይሰራል ብሏል፡፡
ተቋሙ ከክፍያ ስርዓት ጋር ተያይዞ ለቅድመ ክፍያ ካርድ ቆጣሪ ተጠቃሚ ደንበኞች የክፍያ እና የኢነርጂ ሽያጭ ስርዓቱን ይበልጥ ቀላል እና ምቹ ለማድረግ ዩኒፋይድ ፕሪፔይመንት የተሰኘ ፕሮጀክት ቀርጾ ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡