በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ እና እየተገነቡ የሚገኙ ሪዞርቶች የአካባቢዎቹን ጸጋ እንዲለዩ ከማድረግ ባለፈ የሃገሪቱን የቱሪዝም መዳረሻዎች እንደሚያሳድጉ የተለያዩ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት ገለጹ።
ከተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች የተወጣጡ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፖርቲ አባላት የጨበራ የዝሆን ዳና ሎጅ ጎብኝተዋል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ኮንታ ዞን የተገነባው ጨበራ የዝሆን ዳና ሎጅ ለጭስ አልባው ኢንዱስትሪ መጎልበት ከፍተኛ አበርክቶ ያለው መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ተናግረዋል።
እምቅ ሀብቶችን በመለየት የሀገርን እና የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንጻርም አበርክቶዉጰየላቀ ነው ብለዋል።
መንግስት የሚያከናውናቸውን የልማት ስራዎች መደገፍ እና ማበረታታት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚጠበቅ መሆኑን የጠቆሙት አስተያየት ሰጪዎች በሀሳብ የበላይነት በማመን ለሀገር ብልጽግና በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ አጽንዖት ሰጥተዋል።
ጨበራ የዝሆን ዳና ሎጅ በገበታ ለሀገር ከተገነቡ ቅንጡ ሎጆች መካከል የሚጠቀስ ሲሆን ሎጁ የመኝታ፣ የምግብና የመጠጥ አገልግሎቶችን እንዲሁም የተለያዩ የመዝናኛ አማራጮችን በውስጡ ያካተተ ነው።
የሀገራት መሪዎችና የተለያዩ ጎብኚዎችን ማስተናገድ የሚችሉ በቂ አማራጮች እና ምቹ ሁኔታዎች የተሟሉለት ሲሆን ከአካባቢውና ከሀገሪቱ ባህላዊ ይዘት ጋር ተሳስሮ የተገነባው የዝሆን ዳና ሎጅ በተለይም በጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ብቻ የሚገኘውን የአፍሪካ ዝሆን ጨምሮ የተለያዩ እንስሳትን፣ አዕዋፍንና የተፈጥሮ ሀብቶችን በዉስጡ ያካተተ ነው።
በሃብታሙ ሙለታ