ትምህርት ለሀገር እድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የማይተካ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ

You are currently viewing ትምህርት ለሀገር እድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የማይተካ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ

AMN- ሰኔ 15/2017 ዓ.ም

ትምህርት ለሀገር እድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የማይተካ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።

ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 989 ተማሪዎች በዛሬው ዕለት አስመርቋል፡፡

በምረቃ መርሐ-ግብሩ በክበር እንግድነት የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ትምህርት በዓለማችን ከፍተኛ እድገት ላይ ደርሰው የምናያቸው ሀገራት፣ የልእልናቸው ዋነኛው ምክንያት ነው ብለዋል፡፡

ይህም የትምህርት ስርዓታቸውን በአግባቡ በመቅረጻቸው እና በቀረጹትም ልክ በመተግበራቸው መሆኑንም አብራርተዋል።

ኢትዮጵያም እያጋጠሟት ያሉ ዘርፈብዙ ፈተናዎችን፣ በድል እያለፈች መሆኑን በመግለጽ፣ ወደ ብልጽግና የምታደርገውን ጉዞ ማሳካት የምትችለው ለትምህርቱ ዘርፍ በሚሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ነው ብለዋል፡፡

ለዚህም እውን መሆን ሁሉም ዜጎች፣ የመንግስት አካላት እንዲሁም ለሎች ባለድርሻ አካላት ሁሉ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ እና ሲረባረቡ መሆኑን አስረግጠዋል።

ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ በነበራቸው ቆይታ የሀገርን እና የህዝብን አደራ የሚተገብሩ እና ብቁ ዜጋ እንዲሆኑ የሚያስችላቸውን እውቀት፣ ክህሎት እና እሴቶች እንደጨበጡ እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ትምህርት ትውልድን የሚቀርጽ እና የሚያንጽ መሳሪያ መሆኑን የገለጹት ከንቲባ አዳነች፣ መማር የአስተሳሰብ እና የአሰራር ለውጥ ለማምጣት በመሆኑ፣ የትምህርት ባለሞያነትም ትውልድን በማነጽ፣ ሀገርን ለመገንባት የማይተካ ትልቅ ኃላፊነት መሆን ይገባዋል በማለት ተናግረዋል።

ምክንያታዊነት፣ ሰላም ወዳድነት፣ ሥራ ፈጣሪነት፣ ሁሌም ተማሪነት፣ ግብ ተኮርነት፣ ጠንካራ ተልእኮ ላይ የማትኮር ብቃት እና ዝግጁነት የየእለት ተእለት መመሪያችሁ እንዲሆን እመክራለሁ ብለዋል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review