ትላንት ሰኔ 15 ቀን 2017 ዓ.ም ከሌሊቱ 9:05 ሰዓት ላይ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ-ከተማ ወረዳ 6 ሳሪስ በአንድ ፔንሲዎን በተነሳ የእሳት አደጋ ሁለት ሰዎች በጪስ ታፍነዉ ህይወታቸዉ ማለፉን የአዲስ አበባ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
በአዲስ አበባ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ የሆኑት አቶ ንጋቱ ማሞ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ እንደተናገሩት የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በአደረጉት ርብርብ በፔንሲዮን በክፍል ዉስጥ ተኝተዉ የነበሩ ስድስት ሰዎችን መታደግ ተችሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የእሳት አደጋዉ ሳይስፋፋ በፍጥነት መቆጣጠር መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በጪስ ታፍነዉ በአንድ ክፍል ዉስጥ ህይወታቸን ያጡት የ30 ዓመት ወንድና የ25 ሴት መሆናቸዉንም የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዉ አቶ ንጋቱ ማሞ ተናግረዋል፡፡
ፔኔሲዮኑ የዉስጥ ክፍሉ እሳትን መቋቋም ከማይቹሉና አደጋን አባባሽ ከሆኑ በቺፑድ እና በጣዉላ የተከፋፈሉ መሆናቸዉ እሳቱ እንዲባባስና ጪስ እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑም ተልጸዋል፡፡
ፔንሲዮኖችና የሆቴል አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች ወይም ባለንብረቶች እንግዶች የሚያርፉባቸዉን ክፍሎች የአደጋ ደህንነት መስፈርትን ያሟሉና የተጠበቁ በማድረግ የደንበኞቻቸዉ ደህንነት በመጠበቅ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸዉ የገለጹት ባለሙያዉ ኮሚሽኑ የአደጋ ደህንነት መስፈርትን በማያሟሉ አገልግሎት መስጫዎች ላይ አስፈላጊዉን ዕርምጃ እንደሚወስድም አሳስበዋል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ