የፌደራል ፖሊስ የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ስምሪት በወሰደባቸው ቀጠናዎች ከሌሎች የፌደራልና የክልል ፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በፀረ-ሰላም ኃይሎች ላይ ጠንካራ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን እና በቀጣይም ይኸው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ አቅጣጫ አስቀምጠዋል::
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ በመላው ሀገሪቱ ስምሪት በወሰደባቸው ቀጠናዎች ያሉትን የፀጥታ ሁኔታዎች ገምግሞ በቀጣይ ትኩረት በሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ መቀመጡን የፌደራል ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጄይላን አብዲ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል ሚዲያ ባደረሱት መልዕክት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ፣ ኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡርን ጨምሮ በሁሉም የሀገራችን መውጫ እና መግቢያ አውራ ጎዳናዎችን ደኅንነት በመጠበቅ የገቢና ወጭ ምርቶች እንቅስቃሴ የተሳለጠ እንዲሆን በተደረገው እጀባና ቋሚ ጥበቃ ጠንካራ ሥራ መሰራቱን ገልፀዋል።
በመሀል ሀገርና በድንበር የሀገራችን አካባቢዎች የሚንቀሳቀሰውን የገቢና ወጭ ኮንትሮባንድ፣ ሕገ-ወጥ የሰዎችና የጦር መሳሪያ ዝውውርን እንዲሁም ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ከመግታት አንፃር የተሠራው ሥራ አመርቂ ውጤቶች የተመዘገቡበት መሆኑ ተገምግሟል፡፡
በቀጣይም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የተለየ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል::
በተለይም በሀገሪቱ ትላልቅ የልማት አውታሮችና መሠረተ ልማቶች ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳይደርስ ጠንካራ ስምሪት በመደርጉ ተቋማት ባቀዱት ልክ ዓመታዊ እቅዳቸውን እያሳኩ መሆኑ ተገምግሟል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ለተልዕኮ ምቹ የሆነ አደረጃጀት የተፈጠረለት መሆኑንና በቀጣይም በተሻለ ደረጃ ተልዕኮውን መወጣት የሚያስችል ቁመና ላይ መሆኑ በግምገማው ተነስቷል::