ግልገል ጊቤ ሦስት በዚህ ዓመት 7 ሺህ ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨቱ ተገለጸ

You are currently viewing ግልገል ጊቤ ሦስት በዚህ ዓመት 7 ሺህ ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨቱ ተገለጸ
  • Post category:ልማት

AMN- ሰኔ 16/2017 ዓ.ም

የግልገል ጊቤ ሦስት ኃይል ማመንጫ ግድብ በዚህ ዓመት 7 ሺህ ጊጋ ዋት ሰዓት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ለኢኮኖሚው እንቅስቃሴ መሳለጥ ጉልህ ሚና መወጣቱን የኃይል ማመንጫ ግድቡ ሥራ አስኪያጅ ሃብታሙ ሰሙ ገልጸዋል።

ኬንያን ጨምሮ ለቀጣናው ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብም ትልቅ ሚና እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።

የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቡ የታዳሽ ኃይልን በማሳደግና የበካይ ጋዝ ልቀትን በመቀነስ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ተገልጿል።

የግልገል ጊቤ ሦስት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ሥራ አስኪያጅ ሀብታሙ ሰሙ፣ ግድቡ በ2009 ዓ.ም ተጠናቅቆ አገልግሎት መጀመሩን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ላይ ከፍተኛውን ድርሻ በመያዝ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ አዎንታዊ ሚና እየተወጣ የሚገኝ ግዙፉ ፕሮጀክት መሆኑንም ገልጸዋል።

ግድቡ 1 ሺህ 870 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው ሲሆን፣ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቀጥሎ ግዙፉ የኃይል ማመንጫ መሆኑን ተናግረዋል።

የግልገል ጊቤ ሦስት ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ የሀገሪቱን የኃይል አቅርቦት 50 በመቶ በመሸፈን ለጎረቤት ሀገራትም ኃይል በማቅረብ ከፍተኛ ሚና እየተወጣ ነው ብለዋል።

የኃይል ማመንጫ ግድቡ የሥራ ሂደትም በኢትዮጵያውያን ብቁ ባለሙያዎች እየተመራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

ግልገል ጊቤ ሦስት እያደገ ለሚገኘው ሀገራዊ የኤሌክትሪክ ፍላጎት ምላሽ በመስጠት ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በዚህ ዓመትም 7 ሺህ ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል በማመንጨት ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ጉልህ ሚና እንደተጫወተ መንገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review