በአዲስ አበባ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ዛሬ ረፋድ ላይ በግምት 3 ሰዓት ገደማ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 በተለምዶ አባሳሙኤል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የትራፊክ አደጋ የሞት እና የአካል ጉዳት ደርሷል፡፡
ከሟቾቹ መካከል የ3 ዓመት ዕድሜ ያለው ህፃን የሚገኝበት ሲሆን፣ በ8 ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን የአዲስ አበባ ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል ሚዲያ ያደረሱት መረጃ አመላክቷል፡፡
አደጋው ሊከሰት የቻለው ከሃይሌ ጋርመንት ወደ ዩኒሳ አደባባይ ይጓዝ የነበረ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-78979 ኢት የሆነ የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት አውቶቡስ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-04273 ኢት ከሆነ ሌላ ከባድ ተሽከርካሪ ጋር በመጋጨቱ እና መንገድ ስቶ ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ በመግባቱ መሆኑን በክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ የትራፊክ አደጋ ምርመራ ማስተባበሪያ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር መርዕድ ደበሌ ተናግረዋል፡፡
አውቶቡሱ ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ ከገባ በኋላ ከዩኒሳ አደባባይ ወደ ሃይሌ ጋርመንት ሲጓዝ ከነበረ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-77970 ኦሮ ከሆነ ዶልፊን ተሽከርካሪ ጋር በመጋጨቱ፣ በዶልፊኑ ውስጥ ከነበሩት ተሳፋሪዎች መካከል አሽከርካሪውን ጨምሮ የዘጠኝ ሰዎች ህይወት ማለፉን ዋና ኢንስፔክተር መርዕድ አስረድተዋል፡፡
ከሟቹቹ መካከል የ3 ዓመት ህፃን እንደሚገኝበት የጠቀሱት ዋና ኢንስፔክተሩ፤ በሌሎች 8 ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በአካባቢው ላይ የቆመ እና በጉዞ ላይ የነበረ ሌሎች ሁለት ተሽከርካሪዎች በአውቶቡሱ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
የአደጋው መንስኤ እየተጣራ እንደሚገኝ ዋና ኢንስፔክተር መርዕድ ደበሌ አስታውቀዋል፡፡