በዓለም ላይ የሚስተዋሉ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን መቋቋምና ፈጥኖ ምላሽ መስጠት የሚችሉ ጠንካራ ተቋማትን መፍጠር እንደሚገባ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ፡፡
ኢትዮጵያ ከሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በትይዩ ያስተናገደቻቸው 10ኛው የአፍሪካ ሕብረት አባል ሀገራት የመንግሥትአገልግሎትና አስተዳደር እና የተመድ የአፍሪካ ቀጣናዊ ፎረም ዛሬ ተጠናቋል።
የመንግሥት ተቋማት ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን ተቋቁመውና በዘመኑ እየተንከባለሉ የመጡ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በመፍታት አካታች፣ ዘላቂ ልማት የሚያመጣ ተጠያቂነትን የሚያሰፍን፣ ሰብዓዊ መብት የሚያከብር፣የህዝቦችን ትብብር የሚያጠናክር ጠንካራ ተቋማትን ለመፍጠር ያለመ ነበር።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ በማጠቃለያ መርሀ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በትይዩ የተካሄዱት ሁለቱም መድረኮች በስኬት መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።
በዓለም ላይ እየተስተዋሉ ላሉ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን መቋቋምና ቀድሞ ምላሽ መስጠት የሚችሉ ጠንካራ ተቅማትን መፍጠር ይገባል ብለዋል።
በመሆኑም ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ያለውን ውስብስብነት ከግምት ያስገባ አዳዲስ ፈጠራዎችና ሞዴሎችን ገቢራዊ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
የመንግሥት አገልግሎት በአፍሪካ ለዘመናት የቆዩ ችግሮችን መፍታት የሚያስችል መሆኑን በመጥቀስ፤ በአገልግሎት ሰጭዎች ላይ የክህሎት፣ የአመራርና የትብብር አቅምን ማጎልበት ለሀገራዊ ሽግግር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
የኮንፍረንሱ ዓላማ የተቋም ግንባታ ብቻ ሳይሆን ለዜጎች ግልፅና ቀልጣፋ አገልግሎት የመስጠት ሀላፊነት ጭምር መሆኑን አንስተዋል።
የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ፅንሰ ሀሳብ ለዜጎች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ከመስጠት የመነጨ መሆኑን ጠቅሰው፤ እስካሁን ባለው ሂደት ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሪፎርም ከአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 እና የተመድ 2030 ዘላቂ የልማት ግቦች ጋር የተሰናሰነ መሆኑን አንስተዋል።
ስብሰባው የመንግሥት አሰራርን በቴክኖሎጂ መደገፍ፣ የሰው ሀይል አስተዳደርን የኢኖቬሽን አገልግሎትን ማቀላጠፍ ዘመኑ የሚጠይቀው ተቋም ለመፍጠር ያግዛል ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ከዚህም ባለፈ ጠንካራ ተቋማዊ አደረጃጀት በመፍጠር ተቋማዊ ተጠያቂነትን ማስፈንና የተሟላ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ልምዶች የተገኙበት መሆኑን ገልጸዋል።