ከጫፍ የደረሰው እና የኢራን ፓርላማ ያፀደቀው የሆርሙዝ ሰርጥ መዘጋት ጉዳይ

You are currently viewing ከጫፍ የደረሰው እና የኢራን ፓርላማ ያፀደቀው የሆርሙዝ ሰርጥ መዘጋት ጉዳይ

AMN- ሰኔ 16/2017 ዓ.ም

የሆርሙዝ ሰርጥ በነዳጅ ዘይት የበለፀጉ የባህረ ሰላጤው ሀገራትን ከህንድ ውቅያኖስ በማስተሳሰር በየቀኑ 20 በመቶ የሚሆነው የዓለም ነዳጅ ይዘዋወርበታል።

ስፋቱ 33 ኪሎ ሜትር ብቻ የሆነው ይህ ሰርጥ በስተሰሜን ኢራንን በስተደቡብ ደግሞ ኦማንን ያዋስናል።

በአብዛኛው የዓለም ኢኮኖሚ አቀጣጣይ የሚባሉት ዘይት፣ ጋዝና የፔትሮኬሚካል ምርቶች በዚሁ የሆርሙዝ ሰርጥ አልፈው ነው ለዓለም የሚዳረሱት።

ቻይና እና ህንድ ሰርጡን በመገልገል የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱ ሀገራት ናቸው።

በተያዘው የፈረንጆቹ 2025 ብቻ ኢራን በሆርሙዝ ሰርጥ በኩል 67 ቢሊየን ዶላር ነዳጅ ኤክስፖርት አድርጋለች።

ወደ ሰርጡ በሚገቡና በሚወጡ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች መካከል ግጭት እንዳይፈጠር የመጓጓዣ መስመሩ በቀጭን ውሃ የተከፈለ ከመሆኑም በላይ ጠንካራ የትራፊክ አስተዳደር ሥርዓት እንዳለው ይገለፃል።

ታዲያ ኢራን ይህን ቀጭን የነዳጅ መተላለፍያ መንገድ ብትዘጋው የዓለም ኢኮኖሚ የመናጋቱ እና የነዳጅ ዋጋ የመጨመሩ ጉዳይ አይቀሬ ይሆናል።

እንደ ቢቢሲ ዘገባ የሰርጡ መዘጋት የራሷን የኢራንን ጎሮሮ ጭምር መዝጋት ይሆናል፣ በሰርጡ ምክንያት የምታፍሰውን ብዙ ቢሊየን ዶላሮችን ያሳጣታልና።

ኢራን ከእስራኤል ጋር በገባችበት ግጭት ምክንያት ሰርጡን ለመዝጋት የያዘችውን ዕቅድ ፓርላማው አፅድቋል።

ነገር ግን ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው የኢራን ጠቅላይ ምክር ቤት ሲያፀድቀው ነው ተብሏል።

አሜሪካም ሰርጡ እንዳይዘጋ በቻይና በኩል የማግባባት ሥራ ላይ መሆኗ ይታወቃል።

በማሬ ቃጦ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review