ከ61ሺህ በላይ የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ህብረተሰቡ መቀላቀላቸዉን ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን አስታወቀ

You are currently viewing ከ61ሺህ በላይ የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ህብረተሰቡ መቀላቀላቸዉን ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን አስታወቀ

AMN ሰኔ 17/2017

ባለፉት ጊዜያት ከ61ሺህ በላይ የቀድሞ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ህብረተሰቡ መቀላቀላቸውን ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ገለጸ።

ኮሚሽኑ ከስዊድን መንግስት ጋር በመተባበር ከትግራይ፣ ከኦሮሚያ፣ ከአማራ፣ ከአፋር እና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ለተውጣጡ የባለድርሻ አካላት የአሠልጣኞች ስልጠና በአዲስ አበባ መስጠት ጀምሯል።

ስልጠናው ታጣቂዎችን በመልሶ ማቋቋም፣ በኢንተርፕርነርሺፕና በስራ ፈጠራ ዙሪያ የሚያተኩር ሲሆን ለሶስት ተከታታይ ቀናት እንደሚቆይም ተጠቁሟል።

በዚሁ ወቅት መልዕክት ያስተላለፉት የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን፤ ኮሚሽኑ የቀድሞ ታጣቂዎችን ወደ ማህበረሰቡ ከመቀላቀል አኳያ በርካታ ስራዎችን ሰርቷል ብለዋል።

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር እና መከላከያን በመወከል ፕሮግራሙን በማስተባበር ላይ የሚገኙት ብርጋዴር ጀነራል ደርቤ መኩሪያ በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ ስራውን ከጀመረ ጊዜ አንስቶ 61ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና እንዲወስዱ በማድረግ ወደ ማህበረሰቡ መቀላቀል መቻሉን ጠቁመዋል።

በዚህ ሂደት በመሣተፍ ላይ ለሚገኙ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።

የቀድሞ ተጣቂዎችን ወደ ማህበረሰቡ መቀላቀልና ማቋቋም የሰላም ግንባታን ውጤታማ ከማድረግ አንጻር ትልቅ ሚና እንዳለውም ጠቁመዋል።

ኮሚሽኑ የቀድሞ ታጣቂዎች በቋሚነት ስራ ፈጥረው ወደ ምርታማነት ህይወታቸው እንዲመለሱ አስፈላጊ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ዛሬ የተጀመረው ስልጠናም ለስራ ዕድል ፈጠራ እና ታጣቂዎች የተረጋጋ ህይወት እንዲመሩ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን መጠቆማቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በቀጣይ ጊዜያትም ሌሎች የቀድሞ ታጣቂዎችን ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀልና የማቋቋም ስራዎች እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review