ሚኒስቴሩ ”የባህል ብልፅግና ለሀገር መንግስት ግንባታ” በሚል መሪ ሀሳብ ሀገር አቀፍ የባህል እና ቋንቋ ንቅናቄ ሰነድ እና የማስፈፀሚያ ስልት ላይ ያተኮረ ውይይት ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ አካሄዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ነፊሳ አልመሀዲ፤ እንዳስታወቁት ከሀምሌ 1 ቀን 2017 እሰከ መስከረም 30/2018 የሚቆይ ሀገር አቀፍ የባህልና ቋንቋ ንቅናቄ ይካሄዳል።
የንቅናቄው አላማ ብዝሀ ባህልና ቋንቋ ለማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካው ያለውን ሚና ለማሳደግ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይ ባህልና ቋንቋ ለሀገር መንግስት ግንባታና ለህዝቦች ትስስር እንዲሁም ለሰላምና እድገት ፈር ቀዳጅ በመሆኑ በአግባቡ መጠቀም ይገባል ብለዋል።
በዚህ ረገድ በንቅናቄው ከሚከናወኑ አበይት ተግባራት መካከል ከቀበሌ ጀምሮ በባህል ዘርፍ ያሉ እሴቶች ጎልተው እንዲወጡ ማስቻል አንዱ መሆኑን አመልክተዋል።
በተጨማሪም የባህል ፌስቲቫሎች በሁሉም ክልሎች በማካሄድ የባህል መገልገያ መሳሪያዎችና ጌጣ ጌጦች እንዲሁም የሽምግልናና የእርቅ ስርዓቶችን ለትውልድ ግንባታ ለማዋል ጥረት እንደሚደረግም ገልፀዋል።
በሀገር አቀፍና በክልል ደረጃ የሚከበሩ ክብረ በአላትን በአግባቡ አጥንቶ በሁሉም መስክ ጥቅም ላይ ከማዋል ረገድ ያሉ ውስንነቶች ለማሻሻል ጭምር ንቅናቄው ያግዛል ብለዋል።
በንቅናቄው ማህበረሰቡን የሚያስተሳስሩ፤ ወንድማማችነትንና እህታማማችነትን የሚያጠናክሩ ውይይቶች እና ኤግዚብሽን በየደረጃው እንደሚካሄድም አስረድተዋል።
እነዚህን እቅዶች ለማስፈፀም የሚያስችል ሰነድ መዘጋጀቱንም ሚኒስትር ዴኤታዋ አስታውቀዋል።
የባህልና ቋንቋ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ተስፋነሽ ተሎሬ (ዶ/ር) በበኩላቸው ዜጎች ባህላዊ እሴቶቻቸውን እንዲጠብቁና እንዲያሳድጉ ሚኒስቴሩ አበክሮ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በተለይ ባህልና ቋንቋ ሀገራዊ መግባባት እንዲጠናከር ያላቸውን ሚና በመገንዘብ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በሚቀጥሉት ሶስት ወራት ሊካሄድ የታሰበው ንቅናቄ ባህላዊ ሀብቶችን ለማዳበር፤ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ለማጠናከር፤ ባህልን ለወል ትርክት ግንባታ ለማዋል እንዲሁም ወጣቶች ባህላቸውን በሚገባ እንዲያውቁና እንዲጠብቁ ገንቢ ሚና እንዳለው ማስረዳታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በመድረኩ ላይ የሚኒስቴሩ ተጠሪ ተቋማት ኃላፊዎች፤ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላትና የሴቶች አደረጃጀቶች ተገኝተዋል።