የ2017 ትምህርት ዘመን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ የሙከራ ፈተና በ109 የመፈተኛ ጣቢያዎች መሰጠቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ገለፀ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ ዲናኦል ጫላ ለኤ ኤም ኤን እንደገለፁት በዛሬው ዕለት በከተማዋ በበይነ መረብ የተሰጠው የ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ የሙከራ ፈተና፤ ከ109 የመፈተኛ ጣቢያዎች ውስጥ 98 በከተማዋ አስተዳደሩ ስር በሚገኙ ተቋማት ሲሆን 11 ደግሞ በዩኒቨርስቲዎች ነው ብለዋል።
በሁሉም ጣቢያ በተመሳሳይ ሰዓት የሙከራ ፈተናው መሰጠቱን ገልፀው ፣ ይህም አቅማችን የሚፈትሽበት እና ተማሪዎችንም ለበይነ መረብ ፈተና እራሳቸውን የሚያዘጋጁበት መሆኑንም ምክትል ኃላፊው ገልጸዋል።
ኤ ኤም ኤን ያነጋገራቸው የሙከራ ፈተናውን የወሰዱ ተማሪዎችም ፈተናው ከወረቀት ነጻ መሆኑ ጊዜ ቆጣቢ ከመሆን ባለፈ ኩረጃን ማስቀረት የሚችል እና በቀላሉ ቴክኖሎጂውን መላመድ እንድንችል ያደረገ ነው ብለዋል።
በከተማዋ ከ13 ሺ በላይ ተማሪዎች በዛሬ ዕለት የሙከራ ፈተናውን የወሰዱ ሲሆን ለዋናው ፈተናም በከተማዋ ላሉ 48 ሺህ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በበይነ መረብ ብቻ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
ቀጣይ ፈተና በሚሰጥበት ዕለት ከወትሮው ለየት ባለ መልኩ ሰዓት ማክበር እና የተማሪ ደንብ ልብስ መልበስ አስገዳጅ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዲናኦል ጫላ ተናግረዋል።
በዳንኤል መላኩ