በአዲስ አበባ ከተማ የ2017ዓ.ም የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል 88.8% ያህሉ 50% እና ከዛ በላይ በማምጣት ወደ ቀጣዩ የክፍል ደረጃ መሸጋገራቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ አስታወቁ፡፡
ኃላፊው በዛሬው እለት የ2017ዓ.ም የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤትን በማስመልከት ለተለያዩ የመንግስትና የግል የመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዘላለም ሙላቱ የ2017 የትምህርት ዘመን የ8ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ የመልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ 70ሺ 525 ተማሪዎች መካከል 62ሺ 639 ተማሪዎች 50 በመቶ እና ከዚያ በላይ በማምጣት ወደ ቀጣይ ክፍል መሸጋገራቸው በመግለጫቸው ይፋ አድርገዋል፡፡
የ2017 የትምህርት ዘመን የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የማለፊያ ውጤት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ አጠቃላይ የካውንስል አባላት ጋር ውይይት በማድረግ የማለፊያ ውጤት 50 በመቶ እንዲሁም ለአካል ጉዳተኞች 45 እና ከዚያ በላይ እንዲሆን መወሰኑንም ገልጸዋል፡፡
በዚህም መሰረት አጠቃላይ ከተፈተኑ 70 ሺህ 525 ተማሪዎች 62 ሺህ 639 ተማሪዎች 50 እና ከዚያ በላይ አምጥተው ማለፋቸውን ነው የቢሮው ሀላፊ ዶ/ር ዘላለም የተናገሩት፡፡
የዘንድሮዉ የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከአምናው የተሻለ ውጤት የተመዘገበበት እና ሲሆን በዚህ ፈተናውን ከወሰዱ ተማሪዎች መከከል 88 ነጥብ 8 በመቶዎቹ አምሳና ከዚያ በላይ በማምጣት ወደ ቀጣዩ ክፍል መሸጋገር ስለመቻላቸው ገልፀዋል፡፡
የዘንድሮው ውጤት ባለፉት 5 አመታት ከተመዘገቡት ከፍተኛው ነው ብለዋል፡፡
መንግስት ለትምህርቱ ዘርፍ በሰጠው ትኩረት በየዓመቱ የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት ከፍተኛ ለውጥን እያመጣ መሆኑን ያነሱት ሀላፊው በዘንድሮው አመት የተመዘገበው ውጤትም ለዚህ አንዱ ማሳያነው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይ በ2017 ዓ.ም የሒሳብና እንግሊዘኛ ትምህርትን ለማሻሻል ተግባራዊ የተደረገው ስትራቴጂም በተማሪዎች ውጤት ላይ አዎታዊ አስተዋፅዖ ማበርከቱን ጠቁመዋል፡፡
በበጀት አመቱ ፈተናውን ከሰጡ 656 ትምህርት ቤቶች መካከል 276 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ማሳለፍ መቻላቸውን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም የመንግስት ትምህርት ቤቶች የቀን 90 ነጥብ 1 በመቶ ማሳለፍ መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡
ውጤቱ ባጠረ ጊዜ ይፋ መደረጉ ተማሪዎች ለቀጣዩ የትምህርት አመት ከወዲሁ በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ሰኔ 3 እና 4 መሰጠቱ ይታወሳል።
በአይናለም አባይነህ እና ራሄል አበበ