የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ከአሜሪካው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ትብብር ኩባንያ ጋር በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራረመ።
የሥምምነት የተደረገው መርሃ-ግብሩ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በተገኙበት በአንጎላ ሉዋንዳ እየተካሄደ ካለው የአፍሪካ አሜሪካ የቢዝነስ ጉባኤ ጎን ለጎን ነው ።
ሥምምነቱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) እና የአሜሪካው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ትብብር ኩባንያ ጋሬት ጊሽ ፈርመውታል።
ሥምምነቱ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ትብብር ተቋም ጋር ከ200 ሚሊየን ዶላር በላይ በሆነ ካፒታል በኢትዮጵያ በሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ለመሰማራት የሚያስችለው መሆኑ ተገልጿል።
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ሥምምነቱ ኢትዮጵያ የምትፈልገውና ከልማት ፕሮግራሟ ጋር አብሮ የሚሄድ ትልቅ የኢንቨስትመንት ሥምምነት መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ እያስመዘገበች ያለውን አዎንታዊ ውጤት ይበልጥ ወደፊት አጠናክሮ ለማስቀጠል ተጨማሪ አቅም እንደሚሆንም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሥምምነቱ ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ አበረታች ውጤት እያስመዘገበች ባለበት ወቅት መፈረሙን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ዛሬ የተደረሰው ሥምምነት በዘርፉ የተመዘገቡ አበረታች መውጤቶችን ለማስቀጠል እንደሚያስችል ጠቅሰው፤ ኩባንያው በኢትዮጵያ የሚያደርገው ተሳትፎ በአፍሪካም ጭምር ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል ተናግረዋል።
የአሜሪካው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ትብብር ተቋም ፕሬዝዳንትና ሥራ አስፈጻሚ ጋሬት ጊሽ በበከላቸው ሥምምነቱ አሜሪካ አፍሪካን በተመለከተ ለማጠናከር ያሰበችውን የንግድና ኢንቨስትመንት ዲፕሎማሲ የተከተለ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህንንም ተከትሎ ተቋሙ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ተሳትፎው ለኢትዮጵያ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ እድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ያላቸውን እምነት መጥቀሳቸውን ኢዜአ ከስፍራው ዘግቧል።