ሰኔ 18/2017 ዓም
ወቅቱ የ2017 የትምህርት ዘመን መጠናቂያ እልፍ ሲልም የቀጣይ አመት የትምህርት ጉዞ መጀመሪያ ምእራፍ ነው።
በዚህ ጉዞ ታድያ በርካታ ወላጆችን የሚያሳስበው ጉዳይ የትምህርት ቤት ምዝገባና ክፍያ ዋነኛው ነው።
ለአዲስ ገቢዎችም ሆነ ለነባር ተማሪዎች የአዲሱ አመት የትምህርት ዘመን ክፍያ ቀደም ባሉት አመታት አሳሳቢ ሆኖ ቆይቷል።

ኤ ኤም ኤን ዲጂታል ሚዲያ አሁንስ ምን ለውጥ አለ ሲል በጉዳዩ ላይ የተማሪ ወላጆችንና የትምህርት ቤት ርዕሰ መምህራንን አነጋግሯል።
በልደታ ካቶሊክ ካቴድራል እና በቅዱስ ገብርኤል ትምህርት ቤቶች ልጆቻቸውን በማስተማር ላይ የሚገኙ ወላጆች፣ ቀደም ባሉት ጊዜያት የግል ትምህርት ቤቶች የአገልግሎት ክፍያ በዘፈቀደ መሆኑ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን ሲያሳድርባቸው እንደቆየ ያብራራሉ።
ዓመቱ ደርሶ ክፍያው እስኪታወቅም ድረስ በከፍተኛ ሀሳብ ውስጥ እንደሚቆዩም ጭምር ይናገራሉ።

ጉዳዩን ከግምት ውስጥ ያስገባው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም፣ የግል ትምህርት ቤቶች ያልተገደበ የአገልግሎት ክፍያ ጭማሪን በመመሪያ እልባት መስጠቱ ወጥ አሰራር እንዲዘረጋ አስችሎታልም ይላሉ።
የመመሪያው መኖር የትምህርት ቤቶችን ህጋዊ መብት ባከበረ መልኩ ነባራዊ ሁኔታውን ከግምት በማስገባት ወላጆችን ካልተገባ ክፍያ ብሎም ከጭቅጭቅ ያደነ እንደሆነ ይናገራሉ።
ከምንም በላይ ደግሞ መቶ ፐርሰንትና ከዛ በላይ ጭማሪ ለሚያደርጉ ትምህርት ቤቶችም ልጓም ያበጀ ነው ብለዋል።
የቅዱስ ገብርኤል ትምህርት ቤት ርእሰ መመህር መብራቱ ተክለሃይማኖት እና የልደታ ካቶሊክ ካቴድራል ርዕሰ መምህር በላይ አባተ፣ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በመመሪያ መደገፉ በጎ ነገር እንደሆነ አንስተዋል።

በተለይም በመመሪያው በየደረጃው የተቀመጠው የክፍያ ጣሪያ ገደብ መኖር የወላጆችን የመክፈል አቅም ያገናዘበ እንዲሆን ያስቻለ እንደሆነ አብራርተዋል።
ጭማሪው በዘፈቀደ የሚደረግ ሳይሆን፣ በመመሪያው መሰረት ወላጆችንና የትምህርት ባለ ድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ መሆኑ በየሁለት ዓመቱ በመተሳሰብና በመግበባት ላይ የተመሰረተ ጭማሪ እንዲኖር ያስቻለ ነው ብለዋል።
ይህም ድምር ውጤቱ በጋራ በመስራት ለትምህርት ጥራትና ውጤት መመዝገብ ፋይዳው የጎላ እንደሆነም አብራርተዋል።
AMN ዲጂታል