የግል ትምህርት ቤቶች የአገልግሎት ክፍያ በወላጆች ይሁንታ እና በተቋማት የጋራ ስምምነት የሚፈፀም መመሆኑ ተገለፀ

You are currently viewing የግል ትምህርት ቤቶች የአገልግሎት ክፍያ በወላጆች ይሁንታ እና በተቋማት የጋራ ስምምነት የሚፈፀም መመሆኑ ተገለፀ

AMN – ሰኔ 18/2017 ዓ.ም

የግል ትምህርት ቤቶች የአገልግሎት ክፍያ በወላጆች ይሁንታ እና በተቋማት የጋራ ስምምነት የሚፈፀም ነው ሲሉ የአዲስ አበባ የትምህርት ስልጠና ጥራትና ቁጥጥር ባለስልጣን ምክትል ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ታጋይቱ አባቡ ገለጸዋል፡፡

የትምህርት ጥራትን በቀጣይነት ለማረጋገጥ እና የወላጆችን የመክፈል ዓቅም ያገናዘበ የግል ትምህርት ቤቶች የአገልግሎት ክፍያ ደንብ በማዘጋጀት በየደረጃው ከሚገኙ አካላት ጋር የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይትትና የግንዛቤ መፈጠር ስራ ሚዲያን ጨምሮ በተለያዩ አግባቦች እየተሰራ መሆኑንም ምክትል ስራ አስኪያጇ ጠቁመዋል፡፡

በዚህም የግል ትምህርት ቤቶች ተወካይና ባለሃብቶች የወላጅ ተማሪዎች ህብረት ተወካዮች እንዲሳተፉ በማድረግ፣ ደንቡን ለማዘጋጀት ገፊ ከሆኑ ምክኒያቶች እና አጠቃላይ የደንቡን አስፈጻጊነት በተመለከተ በጥልቀት ውይይት መደረጉን ነው ያነሱት፡፡

በዚህም ደንቡ መዘጋጀቱ ከዚህ ቀደም የግል ትምህርት ቤቶች ያደርጉት የነበረው ወጥነት የሌለው የክፍያ አጨማመርን የሚያስቀር በህግና በስርአት እንዲመራ የሚያደርግ መሆኑን በውይይቱ የተገኘ ግብአት መሆኑንም ነው የገለፁት፡፡

ይህንን መነሻ በማድረግ በደንቡ አስፈላጊነት ሰፊ የግንዛቤ ማስጨባጫ ስራ መሰራቱን የገለፁት ወይዘሮ ታጋይቱ፣ ደንቡን ወደ ተግባር ለማስገባት ከወላጆች ጋር ውይይት ማድረግ ዋናው ጉዳይ በመሆኑ ባለፉት ቅዳሜና እሁድ በርካታ ትምህርት ቤቶች ላይ ውይይት መደረጉን አንስተዋል፡፡

በውይይት መድረኮቹም ግልፅ ያልሆኑ እና በወላጆች የሚነሱ ጥያቄዎችን በታዛቢነት በተሳተፉ የባለስልጣኑና የአዲስ አበባ ከተማ እስተዳደር ትምህርት ቢሮ ባለሞያዎች ማብራሪያ በመስጠት ግልፅነት የመፍጠር ስራ መሰራቱን አንስተዋል፡፡

አሁን ላይ የተዘጋጀው የግል ትምህርት ቤቶች የአገልግሎት ክፍያ ደንብ፣ ጭማሪ ካደረጉ ሁለት ዓመት የሞላቸው የግል ትምህርት ቤቶች ለወላጆች ጥሪ በማድረግ አብዛኞቹ ውይይት ማድረጋቸውን አንስተው፣ እንደ ባለስልጣኑም ውይይቱ የተሳካ ነበር ብለዋል፡፡

ነገር ግን በተካሄዱ ውይይቶች በቂ ግንዛቤ አለመኖር መስተዋሉን በማንሳት፣ በውይይቱ የተመደቡ ታዛቢዎች በቂ ማብራሪያ መስጠት መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡

በደንቡ የተቀመጠው የክፍያ ስርአት የየትምህርት ቤቶችን ደረጃና ስታንዳርድ መሰረት ያደረገ አንደሆነ በማመመላከትም፣ ትምህርት ቤቶቹ በተቀመጠላቸው የክፍያ እርከን ከዜሮ ጀምሮ የተቀመጠላቸው ጣሪያ ድረስ ከወላጆች ጋር በጋራ በሚደርሱት ውሳኔ ክፍያው የሚወሰን ይሆናል ብለዋል፡፡

ጣራ የተቀመጠው የክፍያ መጠን ስላለ ብቻ ይወሰናል ማለት ባለመሆኑ፣ ለዚህም የወላጆች ውሳኔ ከፍተኛ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

በክፍያ ስርአት አወሳሰን ላይ ተቋሙና ወላጆች የጋራ ውሳኔ ላይ መድረስ ባይችሉ፣ በመጀመሪያ ወላጆች ያቀረቡት ዋጋ እና ትምህርት ቤቱ የሚያቀርበው ምክረ ሃሳብ ለባለስልጣኑ ከቀረበ በኋላ በባለስልጣኑ ምርመራ ተደርጎበት የሚሰጠው ውሳኔ የሚፀና መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ነገር ግን በውሳኔው ቅሬታ ያለው አካል በደንቡ በሰፈረው መሰረት ከባለስልጣኑ እስከ ከንቲባ ፅህፈት ቤት ቅሬታውን በማቅረብ መስተናገድ የሚችልበት አሰራር መዘርጋቱን የአዲስ አበባ የትምህርት ስልጠና ጥራትና ቁጥጥር ባለስልጣን ምክትል ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ታጋይቱ አባቡ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ አብራርተዋል፡፡

AMN ዲጂታል

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review