ህዝቡን የሰላም ባለቤት በማድረግ ወንጀልን ቀድሞ በመከላከልና የህግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ ሰፊ ስራ መሰራቱን የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮዉ የ2017 በጀት ዓመት የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ አፈፃፀም ሪፖርት በመገምገም የ2018 የትኩረት አቅጣጫዎች አስቀምጧል።
የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ በበጀት አመቱ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ትልቅ ችግር ይታይበት የነበረውን የተራ ማስከበር ስራ ከስራና ክህሎት ጋር በጋራ በመስራት ወጥነት ያለው አሰራር መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል፡፡
ህዝቡን የሰላም ባለቤት በማድረግ ወንጀልን ቀድሞ በመከላከልና የህግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ ሰፊ ስራ መሰራቱንም አንስተዋል፡፡
ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ አክለውም የደህንነት ስጋት የሆኑ አዋኪ ችግሮችን በቅንጅት በመስራት መፍታት መቻሉን ጠቅሰው በቀጣይ የህዝቡን ተሳትፎና ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር የመዲናዋን ሰላምና ፀጥታ ዘላቂና አስተማማኝ በሆነ መልኩ የማፅናት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ አማካሪ የሆኑት አቶ ገብሬ ዳኘው በበኩላቸዉ የኩነት ፈቃድ አገልግሎት ፈልገው ወደ አዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ለመጡ 627 ድርጅቶች ፈጣን አገልግሎት መሰጠቱን ገልፀው አመራሩና ሰራተኛው ዕሮብ እና አርብ የአገለግሎት ቀን አክብሮ በመስራት ከፍተኛ መሻሻል በመፈጠሩ የተገልጋይ የርካታ ደረጃን ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በአሸናፊ በላይ