በአንጎላ አዘጋጅነት በተካሄደው የአፍሪካ አሜሪካ የቢዝነስ ጉባኤ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲዋን የሚያጠናክር ውጤታማ ተሳትፎ ማድረጓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
17ኛው የአፍሪካ አሜሪካ የቢዝነስ ጉባኤ በትናንትናው ዕለት ተጠናቋል።
ጉባኤው ኢትዮጵያ ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ጋር የተሰናሰነውን የቢዝነስ ዲፕሎማሲዋን ያጠናከረችበት መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ዘርይሁን አበበ ገልጸዋል።
በጉባኤው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ውጤታማ የሁለትዮሽ ውይይቶች ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ከአንጎላው ፕሬዝዳንትና ከወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀ-መንበር ጆ ሌሬንሶ፤ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት የአፍሪካ ከፍተኛ አማካሪ ማሳድ ቦሎስና የአፍሪካ ኮርፖሬት ካውንስል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሎሪ ሊዘር ጋር መወያየታቸውንም ጠቅሰዋል።
ከዋናው ጉባኤ ጎን ለጎን በነበሩ የተለያዩ መድረኮች ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴን ጨምሮ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ(ዶ/ር) እና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዘለቀ ተመስገን(ዶ/ር) በኩል ተሳትፎ በማድረግ የኢትዮጵያን አቋም ማንጸባረቅ ተችሏል ብለዋል።
በዚህም በተለይም ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን ያሳየችባቸው፣ የዘርፉን የፖሊሲ ማዕቀፍ ያስተዋወቀችበት፣ የአፍሪካና የአሜሪካ የቢዝነስ ትስስር ምን መምሰል እንዳለበት እይታዋን ያካፈለችባቸው መድረኮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና በአሜሪካ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ትብብር መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ሥምምነትም ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ የጀመረቻቸውን ሰፋፊ ጥረቶች ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን አብራርተዋል።
ሥምምነቱ ከሁለት መቶ ሚሊየን ዶላር በላይ የኢንቨስትመንት ካፒታል የያዘ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ኢትዮጵያ የቱርዝም መሰረተ ልማት በማስፋፋትና መዳረሻ ቦታዎችን በማልማት ምቹ ለማድረግ የያዘችውን ውጥን የሚያግዝ መሆኑን ማስረዳታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡