አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እና የአዲስ አበባ ስራና ክህሎት ቢሮ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

You are currently viewing አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እና የአዲስ አበባ ስራና ክህሎት ቢሮ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

AMN-ሰኔ 19/2017 ዓ.ም

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እና የአዲስ አበባ ስራና ክህሎት ቢሮ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት በዛሬው ዕለት ተፈራርመዋል።

ተቋማቱ “የሚሰሩ እጆች ወግ” የተሰኘ የቴሌቪዥን ፕሮግራም በጋራ ለመስራት የተስማሙ ሲሆን ስምምነቱን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥራቱ በየነ እና የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ ተፈራርመዋል።

“የሚሰሩ እጆች ወግ” የቴሌቭዥን ፕሮግራም የመዲናዋን ነዋሪዎች የስራ ባህል ለማዳበር ብሎም በቂ የስራ ዕድል የሚፈጠርበትን መደላድል መፍጠርን ያለመ ነው። ፕሮግራሙ በወር ሁለቴ ጊዜ የሚተላለፍ ሲሆን በእያንዳንዱ ዝግጅት የ45 ደቂቃ ፍጆታ ኖሮት በአስር ወራት ውስጥ የሚጠናቀቅ መሆኑም ታውቋል።

የስራ ባህልን በተመለከተ በነዋሪዎች ዘንድ የአመለካከት ክፍተት ስለመኖሩ ያነሱት የቢሮ ኃላፊው አቶ ጥራቱ በየነ ይህን ችግር ለመቅረፍ በመገናኛ ብዙሃን ነዋሪውን ተደራሽ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።

በዚህም መረጃን በፍጥነት ተደራሽ በማድረግ ተመልካችን እና አድማጭን በማፍራት ለነዋሪዎች ህይወት መሻሻል እና ለከተማዋ እድገት እየተጋ ከሚገኘው አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር ቢሮው አብሮ ለመስራት መምረጡን አብራርተዋል።

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ለትውልድ እየሰራ ያለ ተቋም ስለመሆኑ ያነሱት የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ በበኩላቸው በ”የሚሰሩ እጆች ወግ” ፕሮግራም ወጣቱን ጨምሮ የመዲናዋን ነዋሪ የስራ ባህል በማሳደግ መዲናዋ እያስመዘገበች የምትገኘውን እድገት የሚያሳልጥ ስለመሆኑ ገልፀዋል። ሁለቱም ተቋማት በትውልድ ለትውልድ የሚሰሩ እንደመሆኑ በገራ ለመስራት የተደረሰው ስምምነት ስኬታማ ስራ ለመከወን እንደሚያግዝም ዋና ስራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።

በመቅደስ ደምስ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review