የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ም/ቤት ምርጫ አስፈፃሚ ቦርድ የ2017 የመጅሊስ ምርጫ ምዝገባን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የምርጫ አስፈፃሚ ቦርዱ በመግለጫው የመራጮች ምዝገባ ከነገ ዓርብ ሰኔ 20/2017 ጀምሮ በ315 መስጂዶች እንደሚከናወን የገለፀ ሲሆን መራጮች ለመመዝገብ ሲመጡ በሚመዘገቡበት መስጂድ አካባቢ ነዋሪ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ የነዋሪነት መታወቂያ ይዘው መምጣት እንደሚጠበቅባቸው አስታውቋል ።
ተመራጮች እስከ ምርጫው እለት ድረስ እንደማይታወቁ የተገለፀ ሲሆን ሁሉም ሙስሊም ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ሲመጣ ለመምረጥ እንጂ ለመመረጥ እንዳልሆነ ሊታወቅ እንደሚገባ ነው የተመላከተው።
ምርጫው በአምስት ዘርፎች የሚካሄድ መሆኑን የጠቆሙት የምርጫ አስፈፃሚ ቦርድ ሰብሳቢ ጂብሪል ኡስማን ይህም በኡለሞች፣ በምሁራን፣ በወጣቶች፣ በሴቶች እና በሰራተኛ ማህበረሰብ ዘርፍ የሚካሄድ መሆኑን ገልፀዋል።
መራጮች ከአምስቱ ዘርፎች መመዝገብ የሚችሉት በአንዱ ዘርፍ ብቻ ሲሆን የተገለፀ ሲሆን እንዲሁም ተመዝጋቢዎች ቢያንስ እድሜያቸው 18 አመት የሞላው ሊሆን እንደሚገባ ነው የተጠቆመው ።
የምርጫ ምዝገባው እስከ ሐምሌ 6/2017 ድረስ ባሉ የዕረፍት ቀናት እንደሚከናወን ነው የተገለፀው ።
ሙስሊሙ ማሕበረሰብ ይህንን ዕድል በሚገባ ተጠቅሞ በቀጣዩ ምርጫ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ ተላፏል።
በመሀመድኑር ኡሊ