ኢትዮጵያ በቆይታ ጊዜዋና በመረጃ መሰብሰብ የተሻለ አቅም ያላትን ሦስተኛዋን የመሬት ምልከታ ሳተላይት እያለማች መሆኑን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ኢትዮጵያ ETRSS-01 እና ET-Smart-RSS የተሰኙ ሁለት የመሬት ምልከታ ሳተላይቶችን ከቻይና የሳተላይት ማስወንጨፊያ ጣቢያ ወደ ሕዋ መላኳ ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ ETRSS-02 የሚል ስያሜ የተሰጣትን ሦስተኛዋን የመሬት ምልከታ ሳተላይት በቅርቡ እንደምታመጥቅ መግለጻቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ ኢኒስቲትዩቱ የተለያዩ የሳተላይት መረጃዎችን በማደራጀትና በመተንተን ለሀገር ጥቅም እንዲውል እየሰራ ይገኛል።
በዚሁ መሰረት ሁለቱ ሳተላይቶች በተቀመጠላቸው ጊዜ የተሰጣቸውን ተልዕኮ ማሳካታቸውን ነው ዋና ዳይሬክተሩ የገለጹት።
ከሳተላይቶቹ የተገኙት መረጃዎች ለግብርና፣ ለቱሪዝም፣ ለመሬት አስተዳደር፣ ለተፈጥሮ ሀብት፣ ለአደጋ ስጋት ቅነሳ አና ለሌሎች ስራዎች በግብዓትነት መዋላቸውን አመልክተዋል።
ተቋማትም የወሰዷቸውን መረጃዎች ጥናትና ምርምርን ጨምሮ ለተለያዩ ስራዎቻቸው እየተጠቀሙበት እንደሚገኙ ጨምረው ገልጸዋል።
ሦስተኛዋን የመሬት ምልከታ ሳተላይት ከ12 እስከ 18 ወራት ባለ ጊዜ ውስጥ ለማምጠቅ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
የሳተላይት ቁጥር መጨመር የመረጃ ግኝት እና ወቅታዊነቱም ጭምር እያደገ እንደሚሄድ መናገራቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በተለይም ሦስተኛዋ የመሬት ምልከታ ሳተላይት ቀደም ሲል ከነበሩት የተሻለ አቅም ያላት፣ የቆይታ ጊዜዋም ከፍ ያለ እና የተሻለ መረጃ መስጠት የሚያስችል አቅም ያላት መሆኑን ጠቁመዋል።

See insights and ads
All reactions:
194194