የዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በሀገር አቀፍ ደረጃ ‘በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ’ በሚል መሪቃል መጀመሩ ይታወሳል:: የፓርቲው የሴት ክንፍም በክረምቱ በተለያዩ የበጎ ፈቃድ ስራዎች ለመሰማራት የፌደራል እና ከተማ አስተዳደር ኃላፊዎች በተገኙበት መርሃ ግብሩን በይፋ አስጀምሯል ።
በክረምትም ይሁን በበጋ የበጎ ፈቃድ ስራዎች ላይ የሴቶች ተሳትፎ እያደገ መጥቷል ያሉት የብልፅግና ፓርቲ የሴት ክንፍ ፕሬዝዳንት እና የፌዴረሽን ምክር ቤት ም/ አፈ ጉባኤ ዛራ ሁመድ በዚህ ክረምት በተለያዩ የበጎፈቃድ ስራዎች 3 ሚሊዮን ሴቶችን ለማሳተፍ መታቀዱን ገልፀዋል።
በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የፌደራል ብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ አለማየሁ እጅጉ በከተማዋ ሴቶችን በማሳተፍ እና በአመራርነት በርካታ የልማት ተግባራት መከናወናቸውን ያነሱ ሲሆን ተጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል።
የሴቶችን ጤና ለመጠበቅ በክረምቱ ከሚከናወኑ የበጎ ፈቃድ ስራዎች መካከል አንዱ የማህፀን በር ካንሰር ቅድመ መከላከል ምርመራ ነው ያሉት ደግሞ የኢፌዴሪ ሴቶችና እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂክማ ከይረዲን ናቸው።
የብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ የነበሩ የፖለቲካ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስብራቶች ለመጠገን እና ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ምቹ አደረጃጀቶችን በመዘርገጋት ጠንካራ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።
ሰኔ 5 የተጀመረው የክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እስከ ጳጉሜ 5 ድረስ የሚቀጥል ሲሆን ችግኝ ተከላ፣ የደም ልገሳ፣ የቤት ዕድሳት፣ የማህፀን በር ካንሰር ቅድመ ምርመራ፣ የአረጋውያን እንክብካቤ እና ሌሎች የበጎ ፈቃድ ተግባራት በፓርቲው የሴት ክንፍ አባላት በክረምቱ ይከናወናሉም ተብሏል።
በአሰግድ ኪዳነማሪያም