የአውሮፓ ሀገራት መሪዎች በማዕቀብ፣ በታሪፍ እና በመካከለኛው ምስራቅ ባላቸው ፖሊሲ ጉዳይ ላይ ሊመክሩ ነው

You are currently viewing የአውሮፓ ሀገራት መሪዎች በማዕቀብ፣ በታሪፍ እና በመካከለኛው ምስራቅ ባላቸው ፖሊሲ ጉዳይ ላይ ሊመክሩ ነው

AMN – ሰኔ 19/2017 ዓ.ም

የአውሮፓ ህብረት 27 አባል ሀገራት መሪዎች፣ በሩሲያ ላይ ጥብቅ ማዕቀቦችን ተግባራዊ ለማድረግ፣ ከአሜሪካ ከባድ የሆኑ አዳዲስ ቀረጦችን የሚያስቀር መፍትሄ ለማግኘት፣ እንዲሁም በመካከለኛው ምስራቅ ግጭቶች ላይ ያላቸውን ተፅዕኖ ማጎልበት በሚቻልበት ሁኔታ ለመምከር በብራስልስ ይሰበሰባሉ።

አብዛኞቹ መሪዎች በዛሬው አጭር የኔቶ ጉባኤ ላይ ከተገኙ በኋላ ወደ ስብሰባው እንደሚያቀኑ ይጠበቃል፡፡

የህብረቱ ዓባል ሀገራት የመከላከያ ወጪያቸውን በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ ቃል በመግባት፣ ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት ችለዋል።

በትናንትናው ዕለት ከፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር የመከሩት የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪም፣ ስብሰባውን በቪዲዮ ኮንፈረንስ እንደሚካፈሉ ተገልጿል፡፡

በአሜሪካ የሚመራው የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) በዚህ ሳምንት ዩክሬንን ከቀዳሚ ጉዳይነት ወደ ጎን ተጫዋችነት ማውረዱ አይዘነጋም፡፡

በዚህም በዩክሬን ያለው የሩሲያ ጦርነት የአውሮፓ ህብረት ቀዳሚ ጉዳይ ሆኗል፡፡

ዓባል ሀገራቱም በሩሲያ ላይ 18ኛውን ዙር ከባድ ማዕቀብ መጣልን በተመለከተ የሚወያዩ ይሆናል፡፡

ይህም አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት የነዳጅ ዋጋ ያንራል በማለት የሚቃወሙትን የዘይት ዋጋ ማስተካከያ ማዕቀብ መጣል ሊሆን እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ያቀረቡት ታሪፍ፣ ለ27ቱም አባል ሀገራት የንግድ ስምምነቶችን የመዋዋል ኃላፊነት በተጣለበት የአውሮፓ ህብረት ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው።

በትናንትናው ዕለት ስፔን ለመከላከያ ኃይል ተጨማሪ ወጪ ባለማውጣቷ ውግዘት ያደረሱባት ሲሆን፣ ተጨማሪ ቀረጥ እንደሚጥሉባትም ዝተዋል።

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንትም ከረጅም ጊዜ አጋሮች ጋር የንግድ ጦርነት ውስጥ በመግባታቸው ፕሬዚዳንት ትራምፕን አውግዘዋል።

የአውሮፓ መሪዎች በመካከለኛው ምሥራቅ በተካሄዱ ጦርነቶች ተፅዕኖ ማሳደር አለመቻላቸው አሳስቧቸዋል።

ስለሆነም ህብረቱ ከኢራን ጋር የኒውክሌር መርሐ-ግብሯን በተመለከተ ዲፕሎማሲያዊ ውይይት እንዲታደስ ግፊት ለማድረግ ይመክራል ተብሏል።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review