በሀገራዊ ምክክሩ አለመግባባቶችን በዘላቂነት በመፍታት የተሻለች ሀገር ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ሚና አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሃይማኖት ተቋማት ገለጹ።
ኮሚሽኑ”ለስኬታማ ሀገራዊ ምክክር የሃይማኖት ምሁራን ሚና” በሚል መሪ ሀሳብ ከተለያዩ ሃይማኖት ተቋማት ምሁራን ጋር በአዲስ አበባ ውይይት አድርጓል።
በውይይቱ እስካሁን በሀገራዊ ምክክር የተሳታፊ ልየታና የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ውስጥ የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት ሚና የጎላ እንደነበር ተነስቷል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣትና የህዝቡን አብሮነት ለማጠናከር ምክክር የማይተካ ሚና እንዳለው ነው ያነሱት።
በተለያዩ አጋጣሚዎች የተፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት በሰከነ መንገድ መመካከርና መፍትሔ መስጠት ወቅቱ የሚጠይቀውና የሃይማኖት ተቋማት ዋነኛ አስተምህሮ መሆኑንም ነው አፅንኦት የሰጡት።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትሪያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌልና ሃዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ሃላፊ መልዓከ ሰላም ቀሲስ ዳዊት ያሬድ፥ ሁሉም ቤተ እምነቶች ስለ-መልካም እሴቶች አበክረው እንደሚያስተምሩ ያነሳሉ።
በኢትዮጵያ ያጋጠሙ አለመግባባቶችን ለመፍታትና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ታልሞ የተቋቋመው ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የታለመለትን ዓላማ እንዲመታ ቤተክርስቲያኗ በየመዋቅሯ አበክራ እንደምትሰራ ገልጸዋል።
የእስልምና ሃይማኖት መምህር ዑዝታዝ አቡበከር አህመድ በበኩላቸው፥ የእምነት ተቋማት ስለ አብሮነትና አንድነት በጽኑ የማስተማር ሃይማኖታዊ ግዴታ እንዳለባቸው ጠቅሰዋል።
የታጠቁ ሃይሎችም ወደ ሰላም እንዲመጡና አጀንዳቸውን በሀገራዊ ምክክሩ እንዲያቀርቡ ከማገዝ አኳያ የሃይማኖት አባቶችና ምሁራን ሚናችንን መወጣት ይገባናል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ አገረ ስብከት መምህር አባገብረ መስቀል ሽኩር (ዶ/ር) አለመግባባቶችን በምክክር ለመፍታት ኮሚሽን ተቋቁሞ ሥራ መጀመሩ ለመላው ህዝብ ትልቅ ድል ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር መሃሙድ ድሪር፥ እስካሁን ባለው ሀገራዊ ምክክር ሂደት የሃይማኖት ተቋማት ሚና የጎላ መሆኑን ጠቅሰው፥ በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ መጠቆማቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ በበኩላቸው፥ የሃይማኖት ተቋማት ለሀገር ሰላምና ለህዝቦች አብሮነት መጠናከር ጉልህ አበርክቶ እንዳላቸው በማንሳት፥ ምክክሩ የታለመለትን ግብ እንዲመታ የላቀ ኃላፊነት አለባቸው ነው ያሉት።