ትውልደ እንግሊዛዊው ቻርሊ ቻፕሊን ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ቀደም ብሎ ፊልሞች ያለ ድምፅ በሚሰሩበት ዘመን በዝምታ ትወናው አለም ሁሉ የሚረዳውና የሚስቅለት ተዋናይ ለመሆን በቅቷል።
አስቂኝ አለባበስ፣ አረማመድ እና ያልተጠበቁ ድርጊቶቹ ለበርካቶች የሳቅ ምንጭ መሆን ችሏል።
ምንም እንኳን በ88 ዓመቱ ህይወቱ ቢያልፍም፣ ዘመን አይሽሬ የትወና ብቃቱ ዛሬም ድረስ ተወዳጅነቱ እንደቀጠለ ነው።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሳቅ ምንጩ ቻርሊ ቻፕሊንን ገፀ ባህሪ በመላበስ ወቅቱን የሚዋጁ የጥበብ ስራዎችን የሚያቀርቡ ወጣቶች ተበራክተዋል።
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትያትሪካል አርት ምሩቁ መሀመድ ጌታባልቻ፣ ኢትዮ ቻርሊ ቻፕሊን በሚል ስራዎቹን በራሱ ማህበራዊ ሚዲያ እያቀረበ የሚገኝ ወጣት ነው።
ጥርስ የማያስከድኑ የቻርሊ ቻፕሊንን አረማመድ፣ እንቅስቃሴና ትወና ገና በልጅነቱ መለማመድ የጀመረው መሀመድ፣በዩኒቨርስቲ ቆይታው ባሳየው ብቃት በርካቶች ጠበቅ አርጎ እንዲይዘው የሰጡት አስተያየት ብርታት እንደሆነው ይናገራል።
የዩኒቨርስቲ ቆይታውን ካጠናቀቀም ቦኋላ በራሴ ስራ መፍጠር አለብኝ በሚል ተነሳሽነት ተሰጥዖውን በቲክቶክ ለማቅረብ ወሰነ።
ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልኩን በመጠቀም በራሱ ማህበራዊ ሚዲያ ስራዎቹን መልቀቅ የጀመረው “ኢትዮጵያዊው ቻርሊ ቻፕሊን” ተቀባይነቱ እያደገ መምጣቱን ይናገራል።
ስራው ገቢን እያስገኘለት ሲሆን፣ በተለይም በህፃናትና ወጣት ተመልካቾች ዘንድ ተቀባይነቱ መጨመሩን ያብራራል::
ወጣቶች ባለን ተሰጠጥዖ ስራን ሳንጠብቅ ከሰራን ራሳችንን የማንቀይርበት ምክንያት የለም ይላል።
በሙያው ነገ ላይ የተሻለ ገቢን መፍጠር ህልሙ እንደሆነ የሚኒገረው “ኢትዮጵያዊው ቻርሊ ቻፕሊን”፣ ተስፋ ባለመቁረጥ ደጋግሞ መሞከርን ከኔ ተማሩ ሲል ይናገራል።
በሚካኤል ህሩይ