በመዲናዋ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የሚፈፀሙ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች ህፃናትና እና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ መረጃ አመላከተ፡፡
የሴት ልጅ ግርዛት ያለዕድሜ እና ያለ አቻ ጋብቻ በመዲናዋ የሚፈፀሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች መሆናቸውን በዳሰሳ ጥናት ማረጋገጡን በቢሮው የስርአተ ፆታ ዳይሬክተር ወይዘሮ በረከት በቀለ ገልዋል ፡፡
በጥናቱ በከተማ ደረጃ አራት ክፍለ ከተሞች ላይ 43 ወረዳዎችን ያካለለ የጥናት ዳሰሳ መደረጉን የተናገሩት ዳይሬክተሯ፣ በተለይ አራት ወረዳዎች ላይ የሴት ልጅ ግርዛት እና ያለዕድሜ ጋብቻ መኖሩን ገልፀዋል፡፡
ለዚህም ግለሰዎቹ ከተለያዩ አካባቢዎች እና ማህበረሰብ የመጡ መሆናቸውንና ድርጊቱ ባህላችን ነው ከማለት ባለፈ የኢኮኖሚ ምንጭና መተዳደሪያ አድርገው የሚኖሩ መሆናቸውን ወይዘሮ ገነት በምክንያትነት አንስተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም እነዚህ ግለሰቦች ድርጊቱን በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ጭምር እየተዘዋወሩ የሚፈፅሙ መሆናቸውን በጥናቱ መረጋገጡንም አንስተዋል፡፡
ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በተጨማሪ ዘመኑ ያመጣቸው ሉላዊነት ወይንም ግሎባላይዜሽን የፈጠራቸው ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን መስፋፋት ያጠናከራቸው ፆታዊ የስነ-ልቦና ጥቃቶች መበራከታቸውን ነው ዳይሬክተሯ የገለፁት፡፡
ነባርም ሆነ መጤ መሰል ፆታዊ ጥቃቶችንና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ለመከላከል እና ለመቀነስ እንዲሁም የወጡ ህጎችን ተፈፃሚ እንዲሆን ለማስቻል፣ ቢሮው በከተማ ደረጃ ከተለያዩ ማህበራዊ ተቋማትና የህበረተሰብ ክፍሎት የተካተቱበት የጥቃት ተከላካይ ኮሚቴ በማዋቀር ስራዎች እየሰራ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡
ወይዘሮ ብርሃኔ ጥላሁን እና ወይዘሮ ራሄል መንገሻ የጥቃት ተከላካይ ኮሚቴ አባል ናቸው፣ እንደዚህ ዓይነቱን ያፈነገጠ እና ለሀገርም ሆነ ለዜጎች የማይበጅ ተግባራትን በአካባቢያችን ሲፈፀም ዝም አንልም እንዲሁም እንዲህ ዓይነት ተግባራት በቤተሰባችን ጭምር እንዳይፈፀም ልጆችን በማስተማር እና በማንቃት ማህበራዊ ሃለፊነታችንን እንወጣለን ነው ያሉት፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች ህፃናት እና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ቆንጂት ደበላ በበኩላቸው፣ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጠቃቶችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል እና ችግሩን ለመቅረፍ ከጥቃት ተከላካይ ኮሚቴው እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ በከተማ ደረጃ ህገ-ወጥ ተግባራት የሚፈፀምባቸውን ቦታና አካባባዎች በመለየት ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ስለመደረጉም ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ 141 የሚደርሱ ጎጂ ልማዳዊ ተግባራት መኖራቸው ይገለፃል፡፡
የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የስነ-ህዝብ እና የጤና ጥናት በ2016 ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት፣ በኢትዮጵያ ዕድሚያቸው ከ15 እስከ 49 ከሆኑ ሴቶች መካከል 65.2 በመቶ የሚሆኑት ለግርዛት የተጋለጡ መሆናቸውንና ይህም ሀገሪቱ በአጠቃላይ የሴት ልጅ ግርዛት በተፈፀመባቸው ሴቶች እና ልጃገረዶች ቁጥር ከግብፅ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ የምትገኝ መሆኗን መረጃው አመላክቷል፡፡